አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ከጣሊያን ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ጋር በትብብር እየሰራ ነው - ሳሙኤል ክፍሌ (ዶ/ር) - ኢዜአ አማርኛ
አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ከጣሊያን ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ጋር በትብብር እየሰራ ነው - ሳሙኤል ክፍሌ (ዶ/ር)
አዲስ አበባ፤ ጥር 20/2017(ኢዜአ)፦የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ከ13 በላይ ከሚሆኑ የጣሊያን ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ጋር በምርምርና በመማር ማስተማር ዘርፍ በትብብር እየሰራ መሆኑን የዩኒቨርሲቲው ተጠባባቂ ፕሬዝዳንት ሳሙኤል ክፍሌ(ዶ/ር) ገለጹ።
ተጠባባቂ ፕሬዚዳንቱ ከጣሊያን ከፍተኛ ትምህርትና ምርምር ሚኒስትር አና ማሪያ ጋር ከጣሊያን ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ጋር በትብብር በሚሰራባቸው ጉዳዮች ዙሪያ ተወያይተዋል።
የዩኒቨርሲቲው ተጠባባቂ ፕሬዚዳንት ሳሙኤል ክፍሌ(ዶ/ር)፤ የጣሊያን ከፍተኛ የትምህርት ተቋማትና አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የትብብር ስራዎችን ማጠናከር በሚቻልባቸው ጉዳዮች ዙሪያ ከሚኒስትሯ ጋር ስኬታማ ውይይት ማድረጋቸውን ገልጸዋል።
የጣሊያን ከፍተኛ ትምህርትና ምርምር ሚኒስትር አና ማሪያ በቀዳማዊ ኃይለ-ስላሴ ዘመነ መንግስት በቤተ-መንግስትነት ሲያገለግል በነበረው የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የኢትዮጵያ ጥናት ማዕከል ጉብኝት ማድረጋቸውንም ተናግረዋል።
ጉብኝታቸውም የጥናት ማዕከሉ ታሪካዊ ይዘቱ ተጠብቆ በዘመናዊ መንገድ ዕድሳት ለማድረግ የጣሊያን መንግስት ድጋፍ የሚያደርግበትን ሁኔታ ማመቻቸትን ዓላማ እንዳደረገም ተናግረዋል።
አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ከ13 በላይ ከሚሆኑ የጣሊያን ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ጋር በትብብር እየሰራ እንደሚገኝ ገልጸዋል።
በሚቀጥሉት ወራቶችም ከተጨማሪ የጣሊያን ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ጋር የትብብር ስምምነት በመፈጸም የሁለቱ ሀገራት ዜጎች የትምህርት ተጠቃሚ የሚሆኑበትን ዕድል ለማመቻቸት በትኩረት እየተሰራ መሆኑን አስረድተዋል።
ዩኒቨርሲቲው ከጣሊያን ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ጋር በቴክኖሎጂ፣ በግብርና፣ በሰውሰራሽ አስተውሎት ፣ በጤና እና ሌሎች የትምህርት መስኮች በትብብር እየሰራ እንደሚገኝ ተናግረዋል።
በተለይም ዘመኑ የደረሰበትን የሳይንስና ቴክኖሎጂ ምርምር ታሳቢ በማድረግ በሰውሰራሽ አስተውሎት፣ ሮቦቲክስ፣ በአይሲቲ፣ የአየር ንብረት ተጽዕኖን መቋቋም በሚያስችሉ ጉዳዮች ላይ በትኩረት እንደሚሰሩ ገልጸዋል።
አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ከጣሊያን ዩኒቨርሲቲዎች ጋር የሚያደርገው ትብብር በህዝብ ለህዝብና በዕውቀት ሽግግር ገንቢ ሚና እየተጫወተ እንደሚገኝም አንስተዋል።
በውይይቱ የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ከፍተኛ የስራ ኃላፊዎች፣ በኢትዮጵያ የጣሊያን አምባሳደር አጎስቲኖ ፓሌስ እና የጣሊያን ከፍተኛ ትምህርት እና ምርምር ሚኒስቴር የስራ ኃላፊዎች ተሳትፈዋል።