ቀጥታ፡

ባለፉት አምስት ዓመታት ከሀገር ወጥተው የነበሩ ከ70 በላይ ቅርሶችን ማስመለስ ተችሏል

አዲስ አበባ፤ ጥር 20/2017(ኢዜአ)፦ ባለፉት አምስት ዓመታት በተለያዩ ጊዜያት ከሀገር የወጡ ከ70 በላይ ቅርሶች ወደ ሀገር ቤት እንዲመለሱ መደረጉን የኢትዮጵያ ቅርስ ባለስልጣን ገለፀ።

ምድረ ቀደምት ሀገር ኢትዮጵያ አይነተ ብዙ ተፈጥሯዊና የሰው ሰራሽ ቅርሶች ባለቤት ስትሆን በርካቶቹም  በዓለም ቅርስነት ተመዝግበዋል።

በሌላ በኩል ኢትዮጵያ ተንቀሳቃሽ ታሪካዊ ቅርሶቿ በተለያዩ ዘመናት ከሀገር እየተዘረፉ ወጥተው በተለያዩ አገራት፣ ተቋማትና ግለሰቦች እጅ ይገኛሉ።

በየክፍላተ ዓለሙ የሚገኙ ቅርሶችን ለማስመለስ የሀገር ተቆርቋሪ ምሁራን፣ ተፅዕኖ ፈጣሪና ታዋቂ ሰዎችን ያቀፈ የኢትዮጵያ ቅርሶች አስመላሽ ብሔራዊ ኮሚቴ ተዋቅሮ ሁሉን አቀፍ ጥረት ማድረጉ ተገልጿል።


 

የኢትዮጵያ ቅርስ ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር ረዳት ፕሮፌሰር አበባው አያሌው ለኢዜአ እንዳሉት ባለስልጣኑ ከተንቀሳቃሽ ቁስ እስከ ታሪካዊ ስነ- ሕንጻዎችን ጥበቃና ልማት ስራዎችን እያከናወነ ነው።

በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) ሀሳብ አመንጪነት ብሔራዊ ቅርሶችን ጨምሮ በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች የሚገኙ ቅርሶችን ጥበቃ፣ ዕደሳትና ጥገና እየተደረገ መሆኑን ጠቅሰዋል።

ከቅርስ ጥበቃና ልማት ባሻገር በየዘመናቱ ከሀገር የወጡ ቅርሶችን ለማስመለስ በመንግስትና በብሔራዊ ኮሚቴው የተደረገውን ጥረት ጠቅሰዋል።

በዚህም ባለፉት አምስት ዓመታት ብቻ በተለያዩ ጊዜያት ከሀገር የወጡ ከ70 በላይ ቅርሶችን ማስመለስ እንደተቻለ ተናግረዋል።


 

ቅርሶች ከማንነትና ታሪካዊ መገለጫነታቸው ባሻገር ለቱሪዝም ኢኮኖሚ እመርታ ሁለንተናዊ ፋይዳ ያላቸው የሀገር ውድ ሀብቶች ናቸው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም