ግሩፑ የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎችን ለማምረት አቅዷል - አምባሳደር ሱሌይማን ደደፎ - ኢዜአ አማርኛ
ግሩፑ የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎችን ለማምረት አቅዷል - አምባሳደር ሱሌይማን ደደፎ
አዲስ አበባ፤ ጥር 20/2017(ኢዜአ)፦ የኢትዮ-ኢንጂነሪንግ ግሩፕ በቀጣይ አምስት ዓመታት የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎችን በሀገር ውስጥ ለማምረት ዕቅድ ይዞ እየሰራ መሆኑን የግሩፑ ዋና ስራ አስፈጻሚ አምባሳደር ሱሌይማን ደደፎ ገለጹ።
በኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ በመታገዝ ከውጭ የሚገቡ ምርቶችን በአገር ውስጥ በመተካት የውጭ ምንዛሪ ከማዳን ባሻገር የቴክኖሎጂ ሽግግር ለማምጣት መንግስት ሰፊ ስራ እያከናወነ ይገኛል፡፡
ዘጠኝ አምራች ኢንዱስትሪዎችን ያቀፈው የኢትዮ-ኢንጂነሪግ ግሩፕም የአሌክትሪክ ተሽከርካሪዎችን በሀገር ውስጥ ለማምረት የሚያስችል ዝግጅት እያደረገ መሆኑን አስታውቋል።
የግሩፑ ዋና ስራ አስፈጻሚ አምባሳደር ሱሌይማን ደደፎ ለኢዜአ እንዳሉት ግሩፑ በቀጣዮቹ አምስት ዓመታት የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎችን በሀገር ውስጥ ለማምረት የሚያስችሉ የቅድመ ዝግጅት ስራዎች እየሰራ ነው።
በኢትዮጵያ የኤሌክትሪክ መኪና ባትሪ ማምረቻ ግብዓት የሚሆነው የሊትዬም ማዕድን ኢትዮጵያ ውስጥ በብዛት የሚገኝ ሲሆን እስካሁንም ማዕድኑን በጥሬው ለውጭ ገበያ እየተላከ መሆኑን ገልጸዋል።
ግሩፑ የሊትዬም ባትሪ በሀገር ውስጥ ለማጣራት የሚያስችል ቴክኖሎጂ በማፈላለግ ላይ ይገኛል ብለዋል።
በተለያዩ መስኮች የሰለጠኑና ከፍተኛ ልምድ ያላቸው 550 ኢንጂነሮች ያሉት ግሩፑ፤ የአሌክትሪክ የህዝብ ማመላለሻና አውቶሞቢሎችን በአምስት ዓመታት ውስጥ ለማምረት ዕቅድ ይዞ እየሰራ መሆኑን አረጋግጠዋል።
በታዳሽ ኃይል የሚሰሩ ተሽከርካሪዎች የአካባቢ ብክለት የሚቀንሱና የኢትዮጵያን የአረንጓዴ ኢኮኖሚ ጉዞ የሚግዙ ናቸው ብለዋል።
ግሩፑ የግብርና ማሽነሪዎችን ለአርሶ አደሩ በማሰራጨት ከፍተኛ ሚና እየተጫወተ ስለመሆኑን አውስተዋል።
ተደራሽነቱን ለማስፋት የግብርና ማሽነሪዎች ድህረ ሽያጭ አገልግሎት ማዕከል በሶማሌ ክልል ለማቋቋም ቦታ መረከቡን ገልጸው፤ በቤንሻንጉል ጉምዝ ክልል ሁለተኛ ማዕከል ለመክፈት በሂደት ላይ መሆኑን ገልጸዋል።
35 ፋብሪካዎች ያሏቸውን ዘጠኝ አምራች ኢንዱስትሪዎች ያቀፈው የኢትዮ-ኢንጂነሪግ ግሩፕ በቅርቡ የኢትዮጵያ ኢንቨስመንት ሆልዲንግስን መቀላቀሉ ይታወቃል