ፈረንሳይ ከአትዮጵያ ጋር የልማት ትብብሯን አጠናክራ ትቀጥላለች - አምባሳደር አሌክሲስ ላሜክ - ኢዜአ አማርኛ
ፈረንሳይ ከአትዮጵያ ጋር የልማት ትብብሯን አጠናክራ ትቀጥላለች - አምባሳደር አሌክሲስ ላሜክ
አዲስ አበባ፤ ጥር 20/2017(ኢዜአ)፡- ፈረንሳይ ከአትዮጵያ ጋር ያላትን የልማት ትብብር አጠናክራ ትቀጥላለች ሲሉ በኢትዮጵያ የፈረንሳይ አምባሳደር አሌክሲስ ላሜክ ገለጹ።
ኢትዮጵያ እና ፈረንሳይ ከ100 ዓመታት የዘለለ ታሪካዊ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት አላቸው።
በኢትዮጵያ የመጀመሪያው የምድር ባቡር የተዘረጋው በፈረንሳውያን እገዛ መሆኑም የሀገራቱን የልማት ትብብር ታሪካዊነት ያሳያል።
በቅርቡ የፈረንሳይ ፕሬዝዳንት ኢማኑኤል ማክሮን በኢትዮጵያ ባደረጉት ጉብኝት ከጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) ጋር በትምህርት፣ በባህልና ቅርስ ጥበቃ እንዲሁም በኢኮኖሚ ልማት ዘርፎች በጋራ ለመስራት መስማማታቸውን በኢትዮጵያ የፈረንሳይ አምባሳደር አሌክሲስ ላሜክ አውስተዋል።
የኢትዮጵያ ሀገር በቀል የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ የሀገሪቱን ዕድገት የሚያፋጥንና ሰፊ ራዕይን ያነገበ በመሆኑ ለስኬቱ ፈረንሳይ ድጋፍ ታደርጋለች ብለዋል።
ኢትዮጵያ ለዓለም ሰላምና ለቀጣናው መረጋጋት እየተጫወተች ያለውን ሚናም አምባሳደር ላሜክ አድንቀዋል።
ሽብርተኝነትን መከላከልና በአካባቢው ሰላምን ማፅናት ፋይዳው ለሁሉም የላቀ በመሆኑ ፈረንሳይ ትብብሯን አጠናክራ ትቀጥላለች ብለዋል።
በሌላ በኩል ኢትዮጵያ የባህር በር ለማግኘት እያደረገች ያለው ጥረት ህጋዊ መሰረትና ተቀባይነት ያለው መሆኑንም ገልጸዋል።
ጉዳዩ በዲፕሎማሲያዊ መንገድ ዕልባት እንደሚያገኝ ሙሉ እምነት እንዳላቸውም ጠቅሰዋል።
የባህር በርን በተመለከተ የአውሮፓን ተሞክሮ የጠቀሱት አምባሳደር ላሜክ በአውሮፓ ወደብ የሌላቸው ሀገራት በቀጣናዊና ዓለም አቀፍ የትብብር ማዕቀፍ የባህር በርና የወደብ ተጠቃሚ መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡
ይህ አካሄድ ለኢትዮጵያም የሚሰራ ትክክለኛ አካሄድ መሆኑን ጠቁመው፥ ኢትዮጵያ የባህር በር ለማግኘት የጀመረችውን ጥረት ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ በተለያዩ መንገዶች ሊደግፍ እንደሚችልም ተናግረዋል፡፡