የአንካራው ስምምነትና የኢትዮ- ሶማሊያ አጋርነት - ኢዜአ አማርኛ
የአንካራው ስምምነትና የኢትዮ- ሶማሊያ አጋርነት
በአፍሪካ ቀንድ በስትራቴጂክ አጋርነታቸው ስማቸው ጎልቶ የሚነሳው ኢትዮጵያና ሶማሊያ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ከወደብ ጋር ተያይዞ በመሃከላቸው ተፈጥሮ የነበረውን አለመግባባት ወደ ተርኪዬ አንካራ በመጓዝ በሰላም መቋጨት ችለዋል፡፡ ይህ አካሄድ አፍሪካውያን የራሳቸውን ችግር በራሳቸው መንገድ መፍታት እንደሚችሉ በድጋሚ ያሳዩበት አዲስ የግጭት መፍቻ መንገድ ተደርጎ ሊወሰድ የሚችል ነው፡፡
ከዚህ ቀደም በሶማሊያ የነበረው ውስጣዊ የሰላምና መረጋጋት ችግር ለአልቃይዳንና አልሸባብ አሸባሪ ቡድኖች መጠናከር ጥሩ አጋጣሚ ፈጥሮ ቆይቷል። በቀጣናው የአሸባሪዎች እንቅስቃሴ ለአካባቢው አገራትም ስጋት በመሆኑ በትብብር መስራትን የሚጠይቅ ይሆናል። ለዚህም የኢትዮ - ሶማሊያ ግንኙነት መጠናከር የላቀ ትርጉም እንዳለው ይታመናል።
ከመካከለኛው ምስራቅ አገራት በመቀጠል አፍሪካ በእርስ በርስ ግጭት የምትናጥ አህጉር ሆና ትጠቀሳለች። በአህጉሪቱ አሁን ላይ ከ35 በላይ የእርስ በርስ ግጭቶች መኖራቸው የሚጠቀስ ሲሆን በግጭቱ ውስጥም በርካታ የታጠቁ ሃይሎች ተሳታፊ መሆናቸው ይነገራል።
ጉዳዩን አሳሳቢ የሚያደርገው በቡርኪና ፋሶ፣ ማሊ፣ ሞዛምቢክ ፣ ናይጄሪያና ሶማሊያ የሚስተዋሉ ግጭቶችን የውጭ ሃይሎችም ሲያባብሱት ይስተዋላል። በመሆኑም የውስጥ ሰላምን ማስጠበቅና ቀጣናዊ ትብብርን ማጠናከር ለዘላቂ መፍትሄ ወሳኝ አርምጃ መሆኑ ይታመናል።
በኮሎምቢያ፣ ፊሊፔንስና አፍጋኒስታን ከተከሰቱት ግጭቶች አንጻር በአፍሪካ የሚታዩ ግጭቶችን በንግግር መፍታት ቀላል መሆኑን በተርኪዬ ሀልዱን ዩኒቨርሲቲ የፖለቲካ ሳይንስና ዓለም አቀፍ ግንኙነት ተባባሪ ፕሮፌሰር አህመት ዩሱፍ ይናገራሉ፡፡ ለዚህ ማሳያው ደግሞ ኢትዮጵያና ሶማሊያ ልዩነታቸውን በሰላም ለመፍታት በቅርቡ በአንካራ የደረሱበት ስምነት ነው ይላሉ ፡፡
ቀጣና ዘለል አንድምታ ያለው የአንካራው ስምምነት
"ሁለቱ አገራት የደረሱበት ስምምነት በአፍሪካ ቀንድ ሊፈጠር ይችላል ተብሎ የተፈራውን ግጭት ያረገበ መሆኑን “ ኢማኑኤል ኦያንጎና ቱግሩል ኦጉዛን የተባሉ የአፍሪካ ጉዳይ ፀሃፊዎች ቲአርቲ በተባለ ድረ ገጽ ላይ ባሰፈሩት ጽሁፍ ጠቅሰዋል፡፡
ጉዳዩ በሰላም እልባት ማግኘቱ ያስደሰታቸው የተባበሩት መንግስታት ድርጅት፣ የአፍሪካ ህብረትና ኢጋድ ለሁለቱ አገራትና ለአደራዳሪዋ ለተርክዬ ምስጋናቸውን በማቅረብ እንኳን ደስ ያላችሁ በማለት መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል፡፡
የሶማሊያ ፈተና
በሶማሊያ የሚንቀሳቀሰው አልሸባብ የአፍሪካ ቀንድ አካባቢን የግጭት ማዕከል ለማድረግ በርካታ ሴራዎችን በመጠንሰስ ግጭት ጠማቂነቱን በግልጽ እያሳየ ይገኛል። ከዚህ ባለፈ ወደ ሶማሊያ እግራቸውን በማስገባት ላይ የሚገኙ አለም አቀፍ ተዋንያንና የተለያዩ አገራት ፍላጎታቸውን ለመጫን በሚያደርጉት ጥረት አገሪቱን ውጥረት ውስጥ ከተዋታል፡፡ በዚህ ረገድ በሶማሊያ የሰፈረው ሰላም አስከባሪ ኃይል ፈተና የተጋረጠበት ሲሆን ይህ እሽቅድድም ለአልሸባብ መጠናከር በር ይከፍታል የሚል ስጋት አሳድሯል።
የዚያድ ባሬ መንግስት ከወደቀበት ጊዜ አንስቶ ሶማሊያ በእርስ በርስ ግጭት ስትናጥ ቆይታ በኋላም በአልሸባብ በእጅጉ እየተፈተነች ቢሆንም በተለይም የቁርጥ ቀን ጎረቤቷ ኢትዮጵያ በከፈለችው መስዋእትነት ህልውናዋ ተጠብቆ ቆይቷል። ኢትዮጵያ የሶማሊያን ሰላም ለማስጠበቅ ያሳየችው ቁርጠኝነትና በተግባርም የከፈለችው መስዋእትነት ቀላል የሚባልም አይደለም።
የዲፕሎማሲ ስኬት ከአዲስ አበባ እስከ አንካራ
ክፍተቱን መሙላት
የተባበሩት መንግስታትና የአሜሪካ ሰላም አስከባሪ ሰራዊት አገሪቱን ለቀው ሲወጡ የተፈጠረውን ክፍተት ለመሙላት ግንባር ቀደም ተሰላፊ የነበረችው ኢትዮጵያ መሆኗን ፀሃፊው ያስታውሳሉ ፡፡ እኤአ በ2005 የእስላማዊ ፍርድ ቤት ህብረት በአገሪቱ የሚንቀሳቀሱ የጦር አበጋዞችን ድል በመንሳት እኤአ 2006 ላይ ስልጣኑን እንደተቆጣጠረ አዝሎት የመጣውን ስጋት ለማስወገድ ቀድማ የተገኘችው ኢትዮጵያ ነበረች፡፡ ኢትዮጵያ የአገሪቱን ሰላም በማስከበር ተልዕኮ ላይ ቆይታ እኤአ በ 2009 አገሪቱን ለቃ ስትወጣ የተከፈተውን ቀዳዳ በመጠቀም አልሸባብ የሶማሊያን ደቡባዊ ክፍል በመቆጣጠር የራሱን መንግስት ለማዋቀር በቅቷል፡፡ ቡድኑ እኤአ በ2012 ከአልቃኢዳ ጋር ያለውን አጋርነት በይፋ አደባባይ ካወጣ በኋላ የአለም ስጋት መሆኑ ታውቋል፡፡
አልሸባብ በኢትዮጵያ በደረሰበት ወታደራዊ ሽንፈት ለ18 አመታት በሶማሊያ ብሎም በጎረቤት አገር ኬኒያ ሲያደርስ የነበረውን ጥፋትና ስጋት በእጅጉ መቀነስ ተችሏል፡፡
ባለፉት 20 ዓመታት የሶማሊያን ሰላም በማረጋጋት፤ እንደ አልሸባብ ያሉ አሸባሪ ኃይሎችን በመዋጋትና ቀጣናዊ መረጋጋትን በመፍጠር የኢትዮጵያ ሠራዊትየላቀ ሚናውን መወጣቱን በርካቶች ያነሳሉ። የኢትዮጵያ ታሪካዊ ጠላት የሆኑ ሃይሎች በዓባይ ጉዳይ በተለይም በህዳሴ ግድብ የጀመሩት የማሰናከል ዕርምጃ አልሳካ ሲል በሶማሊያ በኩል ኢትዮጵያ አፍንጫ ሥር ጦር ለማስፈር መፍጨርጨራቸው በኢትዮጵያ ላይ ቀጥተኛ የብሔራዊ ደኅንነትና ጥቅም ሥጋት እንደሚደቅን ይታመናል፡፡ ይህ ደግሞ በአካባቢው ካለው የኃያላን አገሮች ጂኦፖለቲካዊ ጣልቃ ገብነትና ዓለም አቀፍ የፀጥታ ችግር ጋር ተዳምሮ ቀጣናውን የከፋ ቀውስ ውስጥ ሊከት እንደሚችል እየተገለጸ ነው ፡፡
የሶማሊያ የሽግግር መንግሥት ኢትዮጵያ ወታደሮቿን እንድታስገባ ከጠየቀበት ጊዜ ጀምሮ ለአስራ ሰባት ዓመታት ያህል በአፍሪካ ኅብረት ጥላ ስር በሚገኘው የሰላም አስከባሪ ኃይል ኢትዮጵያ ሰራዊቷን አሰማርታ መስዋዕትነት በመክፈል ላይ ትገኛለች።

ኢትዮጵያ በአትሚስ ስር እንዲሁም ከሶማሊያ ጋር ባላት የሁለትዮሽ ስምምነት በብዙ ሺህ የሚቀጠር ሰራዊት በማሰማራት ለሶማሊያ ሉዓላዊነትና ለህዝቧቿ ደህንነት በዋጋ የማይታመን ከፍተኛ መስዋዕትነትን ከፍላለች።

የአንካራ ስምምነት
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) እና የሶማሊያው ፕሬዝዳንት ሐሰን ሼኽ ሞሐመድ፤ ታኅሣሥ 2 ቀን 2017 ዓ. ም. በቱርክ፣ አንካራ ስምምነት መፈረማቸው ይታወሳል።
ስምምነቱ ኢትዮጵያ "በሶማሊያ ሉዓላዊ ሥልጣን ሥር አስተማማኝ፣ ደኅንነቱ የተጠበቀ፣ ዘላቂ የባሕር መተላለፊያ" እንድታገኝ በቅርበት እንደሚሠሩ ተጠቅሷል። ከዚህ ባለፈ ውይይቱ ባለፈው አንድ ዓመት በሶማሊያ እና በኢትዮጵያ መካከል የተፈጠረውን አለመግባባት ለመፍታት ማስቻሉን አመልከተዋል።
የኢትዮጵያ የባሕር የማግኘት ፍላጎት ጎረቤቶቻችንን ጭምር የሚጠቅም ሰላማዊ ጥረት ነው። ይህ ፍላጎት በትብብር መንፈስ እንጂ በጥርጣሬ ሊታይ አይገባውም" ሲሉ የአገራቸውን ፍላጎት ገልጸዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ጨምረውም "ገንቢ ውይይት" ኢትዮጵያ እና ሶማሊያን "በትብብር፣ በወዳጅነት እና በጠላትነት ሳይሆን በጋራ ለመሥራት ከሚኖር ፈቃደኝነት ጋር ወደ ቀጣዩ ዓመት ያሸጋግራል" ብለዋል።
በኢትዮጵያና ሶማሊያ መካከል አንካራ ላይ የተደረሰው ስምምነት ከጋራ የኢኮኖሚ ተጠቃሚነት ባሻገር አልሸባበን በጋራ ለመዋጋት ከፍተኛ አስተዋጽኦ አለው፡፡ አልሸባብ አሁን ላይ የሶማሊያና ኢትዮጵያ ብሎም የቀጣናው ስጋት መሆኑን ሁሉም ያውቀዋል፡፡

በመሆኑም በአካባቢው ዘላቂ ሰላም ማስፈን የሚቻለው የጋራ ራዕይ በማንገብና በመከባበር ላይ የተመሰረተ ግንኙነትን በማጽናት ሲቻል መሆኑን በተርኪዬ ሀልዱን ዩኒቨርሲቲ የፖለቲካል ሳይንስና ዓለም አቀፍ ግንኙነት ተባባሪ ፕሮፌሰር አህመት ዩሱፍ ለቲአርቲ የሰጡት ማብራሪያ ያመልክታል።