ቀጥታ፡

ርዕደ መሬት በተከሰተባቸው ሦስቱ ወረዳዎች ከ80 ሺህ በላይ ዜጐች በጊዜያዊ መጠለያ ጣቢያዎች ተጠልለው ሰብዓዊ ርዳታ እየቀረበላቸው ነው- የአደጋ ስጋት አመራር ኮሚሽን

አዲስ አበባ፤ ጥር 19/2017(ኢዜአ)፦ በስምሽ ሸለቆ በርዕደ መሬት በተከሰተባቸው ሦስቱ ወረዳዎች ከ80 ሺህ በላይ ዜጐች በጊዜያዊ መጠለያ ጣቢያዎች ተጠልለው ሰብዓዊ ርዳታ እየቀረበላቸው መሆኑን የኢትዮጵያ የአደጋ ስጋት አመራር ኮሚሽን ገለፀ።

ኮሚሽኑ ባወጣው መረጃ እንዳመለከተው በታላቁ ስምጥ ሸለቆ ተፈጥሯዊ እንቅስቃሴ ሳቢያ በተከሰተ ርዕደ መሬት የስጋት ተጋላጮችን ለመታደግ በአፋርና ኦሮሚያ ክልል አዋሳኝ ወረዳዎች ላይ የኢትዮጵያ የአደጋ ስጋት ስራ አመራር ምክር ቤት ባስቀመጠው አቅጣጫ መሰረት የተለያዩ ተግባራት እየከናወኑ ነው።

ርዕደ መሬቱን ተከትሎ በጋራ ግብረ ሀይል የተሰሩ የቅድመ አደጋ መከላከል ስራዎች ውጤታማ መሆናቸውን ገምግመናል- ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ

በአፋር ክልል የስጋት ወረዳዎች በሆኑት አዋሽ ፈንታሌና ዱለሳ ወረዳዎች ከሚገኙ 18 ቀበሌዎች ሰባቱ በርዕደ - መሬት ስጋት ውስጥ የሚገኙ እንደሆኑ ገልጿል።

በሁለቱ ወረዳዎች አስር ሺህ ቤተሰቦች እንደሚኖሩ ያሳወቅ ኮሚሽኑ ይህም በአማካይ 60 ሺህ 36 ዜጎች ለችግሩ ተጋላጭ እንደሆኑ ግምቱን አሳውቋል።

እስከአሁን ከሁለቱ ወረዳዎች የስጋት አካባቢዎችን ለማስለቀቅ በተሰራው ስራ በነፍስ ወከፍ ቁጥር 53 ሺህ 718 ሰዎች ወይም አካባቢውን መልቀቅ ከሚገባው ምጣኔ 90 በመቶ እንደሆኑ ጠቁሟል።

በተመሳሳይ በኦሮሚያ ክልል የርዕደ-መሬቱ ስጋት በሚስተዋልበት የምስራቅ ሸዋ ፈንታሌ ወረዳ የቅድሚያ ቅድሚያ በተሰጣቸው ቀበሌያትን 20 ሺህ 302 ዜጎች አካባቢያቸውን በመልቀቅ ሁሉም በጊዜያዊ መጠለያ እንዲጠለሉ መደረጉን ገልጿል።

ተጨማሪም የስጋት አካባቢ እየሆኑ በመምጣታቸው የተለዩ ሁለት ቀበሌያት ውስጥ የሚገኙ 7 ሺህ 200 ዜጎች ለማስለቀቅ ከማኀበረሰቡ ጋር እየተሰራ ይገኛል ብሏል፡፡

በአጠቃላይ በሁለቱ ክልሎች በሚገኙ ሶስት ወረዳዎች እስከዛሬ ጥር 19 ቀን 2017 ዓ.ም ድረስ 80 ሺህ በላይ ዜጐች በጊዜያዊ መጠለያ ጣቢያ ስለመጠለላቸው አሳውቋል።

ኮሚሽኑ ለአደጋ ተጋላጭ ለሆኑና ከመኖሪያ ቀዬያቸው ለተነሱ ህብረተሰብ ክፍሎች ክልሎች እና ማኀበረሰቡ ከሚያደርጉት ድጋፍ በተጨማሪ ለጉዳት ተጋላጭ ወገኖች የሚውል 282 ሚሊዮን ብር የሚያወጣ ምግብ ነክና ምግብ ነክ ያልሆኑ ሰብዓዊ ድጋፎች ተደራሽ እየተደረጉ መሆኑን ጠቅሷል።

ከኮሚሽኑ በተጨማሪ በፌዴራል ሴክተር መስሪያ ቤቶች፣ በክልሉ መንግስት፣ አጋር አካላት፣ ማህበረሰቡና ልዩ ልዩ ማህበራት አማካኝነት ልዩ ልዩ ሰብዓዊ ርዳታ ድጋፎች እየቀረቡ መሆኑን አረጋግጧል።

በተመሳሳይ ከትምህርት ገበታቸው የተፈናቀሉ 1 ሺህ 542 ህፃናትን በሌሎች አካባቢዎች በሚገኙ ትምህርት ቤቶች ትምህርታቸውን እንዲቀጥሉ መደረጉን ነው የገለጸው።

ኮሚሽኑ ከዚህ በፊት ከርዕደ-መሬት በፊት፣ በርዕደ-መሬት ወቅትና፣ ከዕርደ-መሬት በኋላ መደረግ ስለሚገባቸው ጥንቃቄዎች የተላለፉ መልዕክቶችን በውል በመገንዘብና በማኀበረሰብ ደረጃ በመወያየት ተግባራዊ ማድረግ እንደሚገባ አሳስቧል።

በአፋር ክልል አዋሽ ፈንታሌ እና ዱለቻ ወረዳዎች እንዲሁም በኦሮሚያ ክልል ፈንታሌ ወረዳ የርዕደ- መሬት ክስተት የተፈጥሮ የቅድመ ማስጠንቀቂያ ደውልን ተከተሎ መንግስት የተለያዩ ስራዎችን እያከናወነ ይገኛል - የኢትዮጵያ አደጋ ስጋት ስራ አመራር ኮሚሽን

በማኀበረሰብ፣ በቤተሰብና በግለሰብ ደረጃ ከስጋት አካባቢ ሳያቅማሙ መልቀቅ፣ አካባቢውን ከየትኛውም ሰውና እንስሳት ንክኪ መከለል፤ በሳይንሳዊ ምክረ-ሐሳብ በተለዩ ቦታዎች ብቻ በጊዜያዊ መጠለያ ጣቢያዎች መቆየት እንደሚገባም እንዲሁ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም