ቀጥታ፡

ኢትዮጵያ በዲጅታል የታገዘ የመድሃኒት አቅርቦትና ስርጭትን እየተገበረች ነው-ዶክተር መቅደስ ዳባ

አዲስ አበባ፤ ጥር 19/2017(ኢዜአ)፡-ኢትዮጵያ በዲጅታል የታገዘ ግልፅና ቀልጣፋ የመድሃኒት አቅርቦትና ስርጭትን እየተገበረች መሆኑን የጤና ሚኒስትር ዶክተር መቅደስ ዳባ ገለጹ።

የተለያዩ ዓለም አቀፍ አጋር ድርጅቶች የኢትዮጵያ መደኃኒት አቅራቢ አገልግሎትን የአሰራር ስርዓት ተዘዋውረው ተመልክተዋል።


 

የጤና ሚኒስትር ዶክተር መቅደስ ዳባ እንደገለጹት፤ የጤና አገልግሎት አሰጣጥን ለማሻሻል ከፖሊሲ ጀምሮ በርካታ ለውጦች ተደርገዋል።፡

የዲጂታል ስርዓትን በመዘርጋት ግልፅና ተጠያቂነትን ያሰፈነ አሰራር መተግበር መጀመሩንም ጠቅሰዋል።

በተለይም በመድሃኒት አቅርቦትና ስርጭት ላይ ይስተዋሉ የነበሩ ችግሮችን የሚቀርፍ የቴክኖሎጂ ስርዓት በመተግበር ቀልጣፋ የስርጭት ሰንሰለት መፈጠሩን ጠቁመዋል።

የመድሃኒት ቆጠራና የስርጭት ጊዜ እንዳይጓተት እየተደረገ መሆኑንም ገልጸዋል።


 

የኢትዮጵያ መድሃኒት አቅራቢ አገልግሎት ዋና ዳይሬክተር ዶክተር አብዱልቃድር ገልገሎ በበኩላቸው፤ አገልግሎቱ በሀገሪቱ ለ18 ሺህ የጤና ተቋማት የመድሃኒት አቅርቦትና ስርጭት አገልግሎት እየሰጠ ነው ብለዋል።

አጋር ድርጅቶችም የኤች አይ ቪ ኤድስ፣ የወባ፣ የቲቢና መሰል በሽታዎች ላይ መድሃኒቶችን ድጋፍ እያደረጉ መሆኑን ጠቅሰዋል።

የዛሬው የጉብኝትም የአገልግሎቱን አሰራር፣ የመድሃኒት አያያዝና ስርጭት በማየት ትብብርን ማጠናከርን ያለመ ነው ብለዋል።

አገልግሎቱ መዲኃኒቶችን በቀጥታ ለጤና ተቋማት የሚያደርስበት አዲስ አሰራር መዘርጋቱን ጠቅሰው፥ ይህም መድሃኒቱ የትና በማን እጅ እንደሚገኝ የሚያሳውቅ እንዲሁም ለታካሚዎች ወዲያውኑ እንዲደርስ የሚያስችል መሆኑን ገልጸዋል።


 

በጉበኝቱ ከተሳተፉ አጋር ድርጅቶች ኃላፊዎች መካከል የጋቪ ጥምረት የሀገራት የክትባት አቅርቦት ዋና ኦፊሰር ታባኒ ማፎሳ፥ ኢትዮጵያ ዘመናዊ የመድሃኒት አያያዝና ስርጭት ሰንሰለት መገንባቷ የሚደነቅ ነው ብለዋል።


 

የግሎባል ፈንድ የድጋፍ አስተዳደር ዲቪዥን ኃላፊ ማርክ ኤዲንግተን፥ የኢትዮጵያ መድሃኒት አቅራቢ አገልግሎት ከአምስት ዓመታት በፊት ከሚያውቁት በእጅጉ የላቀ አሰራር ዘርግቶ መመልከታቸውን ጠቅሰዋል።

አገልግሎቱ ከፍተኛ ለውጥና መሻሻል ላይ መሆኑንም ገልጸው፥ በቀጣይ ከኢትዮጵያ ጋር ያላቸውን አጋርነት አጠናክረው እንደሚቀጥሉ ጠቁመዋል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም