በዓለም አቀፉ ዓመታዊ የቁርዓን ውድድር የሚሳተፉ እንግዶች አዲስ አበበ እየገቡ ነው - ኢዜአ አማርኛ
በዓለም አቀፉ ዓመታዊ የቁርዓን ውድድር የሚሳተፉ እንግዶች አዲስ አበበ እየገቡ ነው
አዲስ አበባ፤ ጥር 19/2017(ኢዜአ)፡- በኢትዮጵያ በሚካሄደው ዓለምአቀፉ ዓመታዊ የቁርዓን ውድድር የሚሳተፉ እንግዶች አዲስ አበበ እየገቡ ነው።
ከውድድሩ በተጨማሪ ተወዳዳሪዎቹ በኢትዮጵያ የሚገኙ የቱሪስት መስህብ ስፍራዎችን ይጎበኛሉ።
ውድድሩ በዘይድ ኢብን ሳቢት የቁርዓን ማኅበርና በኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት የተዘጋጀው ነው።
ኢትዮጵያ ዓለም አቀፍ ጉባኤዎችን የማስተናገድ አቅሟ እያደገ በመምጣቱ በርካታ ዓለም አቀፍ እና አህጉራዊ ጉባኤዎችን እያስተናገደች ትገኛለች።
በቱሪስት መዳረሻ መሰረተ ልማት ግንባታ ላይ በተሰሩ በርካታ ስራዎችም ለጉብኝት ወደ ኢትዮጵያ የሚመጡና ለተለያዩ ዓለም አቀፍ እና አህጉራዊ ጉባኤዎች እና ውድድሮች የሚመጡ እንግዶች የቆይታ ጊዜያቸውን በማራዘም የቱሪስት መዳረሻ ስፍራዎችን እየጎበኙ ይገኛሉ።
ኢትዮጵያ መሰል ዓለም አቀፍ የውድድር መርሃ ግብሮችንና ጉባኤዎችን በማስተናገድ የኮንፍረንስ ቱሪዝምን ማሳደግ የሚያስችል ትልቅ አቅም ገንብታለች።
ለዚህም ባለፉት የለውጥ ዓመታት በቱሪዝም ዘርፍ አዳዲስ የቱሪስት መዳረሻ ስፍራዎችን ከማልማት ባለፈ ነባሮችን የማደስ ስራዎች ተሰርተዋል።
በዚህም ኢትዮጵያን ለመጎብኘት ምርጫቸው ያደረጉ ጎብኚዎች ቁጥር እየጨመረ እንዲመጣ በማድረጉ ከአምስት ዓመታት ወዲህ የጎብኚዎች ቁጥር በ40 በመቶ ማደጉንና በአፍሪካ የጎብኚዎች ቁጥር በከፍተኛ ሁኔታ ከጨመረባቸው ሀገራት መካከል ቀዳሚ ደረጃ ላይ ተቀምጣለች።
በዚህ ዓለም አቀፍ ዓመታዊ የቁርዓን ውድድር ላይ የሚሳተፉ እንግዶችም በቆይታቸው በኢትዮጵያ የሚገኙ የተለያዩ የቱሪስት መስህብ ስፍራዎችን እንደሚጎበኙ አዘጋጆቹ ገልጸዋል።
የዘይድ ኢብን ሳቢት የቁርዓን ማኅበር ፕሬዝዳንትና የኢትዮጵያ ዓለም አቀፍ የቁርዓንና የአዛን ውድድር ዋና ኃላፊ ዶክተር ኑረዲን ቃሲም፤ ውድድሩ ከጥር 21 እስከ 25/2017 ዓ.ም እንደሚካሄድ አስታውቀዋል።
ኢትዮጵያን የሚወክሉ 2 ወንድና 1 ሴት ተወዳዳሪዎች መለየታቸውንም ጨምረው ተናግረዋል።
በውድድሩም ከአፍሪካ፣ ከመካከለኛው ምስራቅ፣ ከኤሲያ፣ ከአውሮፓ፣ ከአሜሪካ በአጠቃላይ ከ60 ሀገራት የተውጣጡ ተወዳዳሪዎች የሚሳተፉ ሲሆን ተወዳዳሪዎቹ አዲስ አበባ እየገቡ መሆኑን ገልጸዋል።
የፓርላማ አባላት፣ ኢንቨስተሮች፣ አምባሳደሮችና ሌሎች አካላት በውድድሩ ላይ ይታደማሉ ሲሉም አስታውቀዋል።
ከውድድሩ በተጨማሪ ተወዳዳሪዎቹ በኢትዮጵያ የሚገኙ የቱሪስት መስህብ ስፍራዎችን እንደሚጎበኙ ነው ዶክተር ኑረዲን ቃሲም ጨምረው የተናገሩት።