ቀጥታ፡

ኢትዮጵያ የምስራቅ አፍሪካ የፖሊስ አዛዦች ህብረት ድርጅት ጠቅላላ ጉባዔ ላይ እየተሳተፈች ነው

አዲስ አበባ፤ ጥር 19/2017(ኢዜአ)፦የኢትዮጵያ ፌዴራል ፖሊስ በሩዋንዳ ኪጋሊ እየተካሄደ በሚገኘው 26ኛው የምስራቅ አፍሪካ የፖሊስ አዛዦች ህብረት ድርጅት ዓመታዊ ጠቅላላ ጉባኤ ላይ እየተሳተፈ ይገኛል።

የኢትዮጵያ ፌዴራል ፖሊስ ወንጀል ምርመራ ጠቅላይ መምሪያ አዛዥ ምክትል ኮሚሽነር ጀነራል ዘላለም መንግስቴ በጠቅላላ ጉባኤው ላይ ተሳታፊ ሆነዋል።


 

ምክትል ኮሚሽነር ጀነራሉ በዓመታዊ ጠቅላላ ጉባኤው ላይ የኢትዮጵያ ፌዴራል ፖሊስ ልምድና ተሞክሮዎችን ለሌሎች የምስራቅ አፍሪካ ሀገራት የፖሊስ አዛዦች እንደሚያካፍሉም ይጠበቃል።

ሽብርተኝነትን ጨምሮ ከጊዜ ወደ ጊዜ እያደጉ የመጡ ድንበር ተሻጋሪ ወንጀሎችን በጋራ ለመከላከል በሚያስችሉ ስትራቴጂዎች ላይም ይመክራሉ።

በዓመታዊ ጠቅላላ ጉባኤው ላይ የምስራቅ አፍሪካ አባል ሀገራት አንገብጋቢ በሆኑ የፀጥታ ተግዳሮቶች ላይ እንደሚወያዩ ተገልጿል።


 

ጉባዔው ሀገራቱ የጋራ ስትራቴጂዎችን በመንደፍና እየተፈጠሩ ያሉ ተለዋዋጭ ወንጀሎች ላይ በመምከር ችግሮቹን የሚፈቱበት የትብብር ማዕቀፍ መፍጠር እንደሚያስችል ከኢትዮጵያ ፌዴራል ፖሊስ የተገኘው መረጃ ያመለክታል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም