ቀጥታ፡

የኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማህበር በኢትዮጵያ የመጀመሪያ የሆነውን የሰብአዊነት ትምህርት ቤት ከፈተ

አዲስ አበባ፤ ጥር 19/2017(ኢዜአ)፡-የኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማህበር በኢትዮጵያ የመጀመሪያ የሆነውን የሰብአዊነት ትምህርት ቤት ከፈተ።

ማህበሩ በዛሬው እለት በስካይ ላይት ሆቴል ባካሔደው መርሃ-ግብር የሰባዓዊነት ትምህርት ቤቱን መከፈት አብስሯል።

በመርኃ ግብሩ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ምክትል አፈ ጉባዔ ሎሚ በዶን ጨምሮ የመንግስት የስራ ሃላፊዎች ፣ መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅት ተወካዮችና አምባሳደሮች ተገኝተዋል።


 

ምክትል አፈ ጉባዔ ሎሚ በዶ በዚሁ ወቅት እንደገለጹት የሰብዓዊነት ትምህርት ቤቱ በሰብዓዊ እርዳታ ዘርፍ የሰለጠነ የሰው ሃብት ለማፍራት የጎላ ሚና ይኖረዋል ፡፡

የኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማህበር ለበርካታ አመታት በተፈጥሮም ሆነ ሰው ሰራሽ ምክያት ጉዳት ለደረሰባቸው ወገኖች ልዩ ልዩ ሰብዓዊ ድጋፎችን ሲያደርግ መቆየቱን ተናግረዋል፡፡

የሰብዓዊነት ትምህርት ቤቱ ሰብዓዊነትን የተላበሰ ትውልድ ለማፍራትና በተለያዩ ምክንያቶች ለሚከሰቱ አደጋዎች ፈጣን ምላሽ ለመስጠት የጎላ ሚና እንደሚኖረውም ገልጸዋል፡፡


 

ማህበሩ የሰብዓዊነት ተግባሩን በበለጠና ሳይንሳዊ በሆነ መንገድ ተደራሽ ለማድረግ እንደሚረዳው ምክትል አፈ ጉባዔዋ ጠቅሰዋል፡፡

በመሆኑም መንግስት ማህበሩ ያቀደውን ተግባር እንዲያሳካ አስፈላጊውን ድጋፍ እንደሚያደርግ አረጋግጠዋል፡፡

የኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማህበር ዋና ጸሃፊ አበራ ሉለሳ በበኩላቸው፤ የትምህርት ቤቱ ዋና አላማ በሰብዓዊነት የታነጸ ትውልድ ማፍራት ነው ብለዋል፡፡


 

በአሁኑ ሰዓት የትምህርት ካሪኩለሙ ተዘጋጅቶ ማለቁንና ከነገ ጀምሮ ምዝገባ የሚካሔድ መሆኑን አመላክተዋል፡፡

ትምህርቱ ሰብዓዊነትን የተመለከቱ ዘጠኝ አይነት ኮርሶች እንዳሉት ጠቅሰው ትምህርቱን በአካል እና በበይነ መረብ መከታተል እንደሚቻል ገልጸዋል፡፡

ትምህርቱ ለአንድ አመት የሚሰጥ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡

ትምህርቱን የሚሰጡት መምህራን ሰብዓዊነት የሚገዳቸው እና በህብረተሰቡ ዘንድ ጥሩ ተቀባይነት ያላቸው መሆኑን ተናግረዋል፡፡

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም