የጤና አገልግሎት ተደራሽነትን ለማስፋት ከአለም አቀፍ አጋር ድርጅቶች ጋር የሚኖረው ትብብር ተጠናክሮ ይቀጥላል - ጤና ሚኒስቴር - ኢዜአ አማርኛ
የጤና አገልግሎት ተደራሽነትን ለማስፋት ከአለም አቀፍ አጋር ድርጅቶች ጋር የሚኖረው ትብብር ተጠናክሮ ይቀጥላል - ጤና ሚኒስቴር
አዲስ አበባ፤ ጥር 19/2017(ኢዜአ)፡- በኢትዮጵያ ጥራትና ፍትሃዊነቱን የጠበቀ የጤና ተደራሽነትን ለማስፋት ከዓለም አቀፍ አጋር ድርጅቶች ጋር የሚኖረው ትብብር ተጠናክሮ እንደሚቀጥል የጤና ሚኒስትር ዶክተር መቅደስ ዳባ ገለጹ።
ዶክተር መቅደስ ዳባ እና የጤና ሚኒስቴር ከፍተኛ የስራ ኃላፊዎች ከዓለም ጤና ድርጅት እና በጤናው ዘርፍ ከሚሰሩ ባለድርሻ አካላት ጋር በአዲስ አበባ ተወያይተዋል።
በውይይቱም ኢትዮጵያ በጤናው ዘርፍ ባከናወነቻቸው ተግባራት የተመዘገቡ ስኬቶችንና የጤና ሚኒስቴር ተቋማዊ መዋቅርና የባለድርሻ አካላት ትብብርን የሚያሳይ የመነሻ ጽሁፍ ቀርቧል።
በዚሁ ጊዜ የጤና ሚኒስትር ዶክተር መቅደስ ዳባ፤ የዜጎችን ጤና ለመጠበቅ የሁሉንም ባለድርሻ አካላት ገንቢ ሚና በማስቀጠል በትብብር እየተሰራ እንደሚገኝ ገልጸዋል።
ከዓለም አቀፍ ተቋማት ጋር ኢትዮጵያ በጤናው ዘርፍ ያስመዘገበቻቸውን ስኬቶች በማስቀጠል የሚያጋጥሙ ችግሮችን መቅረፍ የሚያስችል የትብብር ሥርዓት መዘርጋቱን ተናግረዋል።
በትብብሩ የዜጎችን ተላላፊና ተላላፊ ያልሆኑ የበሽታ ተጋላጭነትን ለመቀነስ በተሰራው ሰፊ ስራ ውጤት መገኘቱን አንስተዋል።
ከዓለም አቀፍ የጤና አጋር አካላት ጋር በተደረገው ውይይት ኢትዮጵያ አህጉራዊ የጤና አጀንዳን ለማሳካት በጤና ፋይናንስና በጤና ፖሊሲ የተሻለ ልምድ እንዳላት መነሳቱን ገልጸዋል።
በአየር ንብረት ለውጥና ተያያዥ ጉዳዮች የሚከሰቱ የበሽታ አይነቶችን ለመከላከል የአጭር፣ የመካከለኛና የረጅም ጊዜ የጤና ሥርዓት በመዘርጋት በትኩረት እየሰራች መሆኗን ተናግረዋል።
ከ35 የሚበልጡ ዓለም አቀፍ ተቋማትና ባለድርሻ አካላቱ በሚኖራቸው ቆይታ ለሌሎች የአፍሪካ ሀገራት ተሞክሮ የሚሆን የመስክ ምልከታ እንደሚያከናውኑም አስታውቀዋል።
ባለድርሻ አካላት በሚኖራቸው ቆይታ ኢትዮጵያ በዘርፉ ያስመዘገበቻቸውን ስኬቶች በማስቀጠል ውስንነቶችን ለማስተካከል ገንቢ ምክረ ሃሳብ እንደሚቀርብ አንስተዋል።
የጤና ፍትሕዊነት፣ ተደራሽነትና ጥራትን በማስፋት በበሽታ መከላከል፣ በታክሞ ማዳን፣ በመድኃኒት አቅርቦት፣ በአገልግሎትና ዲጂታላይዜሽን የተሻሉ ውጤቶች ተመዝግበዋል ነው ያሉት።
የኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄን መነሻ በማድረግ ለህክምና አገልግሎት የሚውሉ መድኃኒቶችና ቁሳቁሶችን በሀገር ውስጥ ለማምረት ልዩ ትኩረት የተሰጠው መሆኑን አንስተዋል።
ለአብነትም ለጤና እና ጤና ነክ የሚያገለግሎ የህክምና መሳሪያዎችን በሀገር ውስጥ ምርት የመተካት ተግባር በትኩረት እየተሰራበት እንደሚገኝ አንስተዋል።
የዓለም ጤና ድርጅትና በጤናው ዘርፍ የሚሰሩ ባለድርሻ አካላት በኢትዮጵያ ለሶስት ቀናት በሚኖራቸው ቆይታ የጤና ተቋማት አገልግሎት አሰጣጥን በተመለከተ የመስክ ምልከታን ጨምሮ ከጤና ሚኒስቴር የስራ ኃላፊዎች ጋር ውይይት እንደሚያደርጉ ይጠበቃል።