ቀጥታ፡

በተለያዩ ሀገራት የሚገኙ ቅርሶችን ለማስመለስ እየተደረጉ ያሉ ጥረቶች ተጠናክረው ይቀጥላሉ - ቱሪዝም ሚኒስቴር

አዲስ አበባ፤ ጥር 19/2017(ኢዜአ)፡- በተለያዩ ሀገራት የሚገኙ ቅርሶችን ለማስመለስ እየተደረጉ ያሉ ጥረቶች ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ የቱሪዝም ሚኒስትር ዴኤታ ስለሺ ግርማ ገለጹ።

የቱሪዝም ሚኒስቴር በአዲስ አበባ የሚገኘው የዩኔስኮ ግንኙነት ጽህፈት ቤት "አዲስ የትብበር ቅጾች እና የአፍሪካ የባህል ሀብት ማስመለስ አህጉራዊ አቀራረብ" በሚል የውይይት መድረክ ተካሂዷል።


 

በመድረኩ የቱሪዝም ሚኒስትር ዴኤታ ስለሺ ግርማን ጨምሮ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የትምህርት፣ የሳይንስ እና ባህል ድርጅት(ዩኔስኮ) የስራ ሀላፊዎች እና ሌሎች የአፍሪካ ሀገራት ተሳታፊዎች ታድመዋል።

አቶ ስለሺ ግርማ መድረኩን በከፈቱበት ወቅት እንዳሉት የጉባኤው ዓላማ እ.አ.አ. በ1970 ቅርሶችን ከተለያዩ ሀገራት ለማስመለስ የተደረገውን ስምምነት ተከትሎ መሆኑን ገልጸዋል።

የተፈረመው ስምምነት ላለፉት አመታት ከበርካታ የዓለም ሀገራት የተዘረፉ እና የተዘዋወሩ ቅርሶችን ወደ ባለቤት ሀገር የመመለስ ዓላማ ያለው እንደሆነም ተናግረዋል።

ይህ ጥረት ከሞላ ጎደል ውጤት የተገኘበት ቢሆንም በቂ አለመሆኑን አንስተዋል።

በርካታ የአፍሪካ ሀገራት በቅኝ ግዛት እንደነበሩ አስታውሰው አብዛኛው ቅርሳቸው ከሀገራቸው ውጭ እንደሚገኙ አመላክተዋል።


 

ኢትዮጵያ በቅኝ ግዛት የተያዘች ሀገር ባትሆንም በተለያዩ ጊዜያት በነበሩ የቅኝ ግዛት ፍላጎት ሙከራዎች በርካታ ቅርሶች ከሀገር እንደወጡባት ጠቁመዋል።

በመድረኩ ቅርሶችን በማስመለስ በኩል ኢትዮጵያ ተጠቃሽ ስራ ካከናወኑ ሀገራት መካከል ተጠቃሽ መሆኗን አንስተዋል።

ባለፉት ዓመታት በርካታ ቅርሶች መመለሳቸውን ገልጸው፤ አሁንም ተጨማሪ ቅርሶችን ለማስመለስ ውይይቶች እየተደረጉ መሆኑን ተናግረዋል።

እንዲሁም ቅርሶችን በአግባቡ ከመያዝ እና ዲጂታላይዝ ከማድረግ አኳያ ውጤታማ ስራ መስራቷን አመላክተዋል።

ለቅርስ ጥበቃ እና ህገወጥ ዝውውርን ለመከላከል አስፈላጊ የሆኑ የህግ ማዕቀፎች በማዘጋጀት እና በመተግበር ውጤታማ ስራ መሰራቱን ጠቁመዋል።

በተለያዩ ምክንያቶች በርካታ የኢትዮጵያ ቅርሶች በተለያዩ ሀገራት ተቋማት እና ግለሰቦች እጅ እንደሚገኙ ተናግረዋል።

እነዚህ ቅርሶችን ለማስመለስ እየተደረጉ ያሉ ጥረቶች ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ አመላክተዋል።

በአፍሪካ ቅርስን የማስመለስ ጥረቶችን ለመደገፍ ትብብርን ማጠናከር የህግ ማዕቀፎችንና የአስፈጻሚ አካላትን ትኩረት ማግኘት እንዳለባቸው አስገንዝበዋል።


 

በተባበሩት መንግስታት ድርጅት የትምህርት፣ የሳይንስ እና ባህል ድርጅት(ዩኔስኮ) የባህል ረዳት ዳይሬክተር ጀነራል ኤርኔስቶ ኦቶኔ ድርጅቱ በኮንቬንሽኑ መሰረት ህገ-ወጥ የቅርስ ዝውውርን እየተከላከለ መሆኑን ገለጸዋል።

እንዲሁም ያልተመለሱ ቅርሶች በሁለትዮሽ ውይይቶች እንዲፈቱ የማሸማገል ስራዎችን እየሰራ መሆኑን ተናግረዋል።

የተለያዩ ቅርሶች ሽያጭ እንዲቆም እንዲሁም በተለያዩ መንገድ እንዲመለሱ እያደረገ መሆኑን ጨምረው ተናግረዋል።


 

በአፍሪካ ህብረት የትምህርት፣ የሳይንስ እና ባህል ድርጅት(ዩኔስኮ) ተወካይ ዶክተር ሪታ ቢሶናውት ባህልና ቅርስ ከዩኔስኮ አምስት ልዩ የትኩረት መስኮች አንዱ መሆኑን ገልጸዋል።

ቅርሶችን መመለስ የዜጎችን ክብር መመለስ መሆኑን ገልጸው ይህ መድረክ ለአፍሪካ አስፈላጊ መሆኑን ጠቁመዋል።

ውይይቱ በጣም ጠቃሚ መሆኑን ገልጸው፤ ከውይይቱ የሚገኙ ምክረ ሀሳቦች በ2025 የአፍሪካ ህብረት ጉባኤ ላይ እንደሚነሱ ያላቸውን እምነት ጠቁመዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም