ቀጥታ፡

ባለፉት ስድስት ወራት 17 ቢሊየን ብር የሚገመቱ መድኃኒቶች ተሰራጭተዋል

አዲስ አበባ፤ጥር 19/2017(ኢዜአ)፦በ2017 በጀት አመት የመጀመሪያዎቹ ስድስት ወራት 17 ቢሊየን ብር የሚገመቱ መድኃኒቶች መሰራጨታቸውን የኢትዮጵያ መድኃኒት አቅራቢ አገልግሎት ገለፀ።

የአገልግሎቱ ዋና ዳይሬክተር አብዱልቃድር ገልገሎ ለኢዜአ እንዳሉት፥ የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያውና የኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ የአገር ውስጥ የመድኃኒት አምራቾችን አቅም ማጠናከር አስችሏል።

በዚህም ከዚህ ቀደም በከፍተኛ የውጭ ምንዛሬ ከውጭ ይገቡ የነበሩ የጓንትና ስሪንጅ ምርቶች በአገር ውስጥ መመረት መጀመሩን ተናግረዋል።

አገልግሎቱ የፋይናንስና የመጋዘን ስርዓቱን በማዘመን የዲጂታል ስርዓት መተግበር መጀመሩንም ገልፀዋል።

መድኃኒቶችን ከአገልግሎቱ ወደጤና ተቋማት ለማድረስ የሚያስችሉ 53 መኪኖች ተገዝተው ለስርጭት ዝግጁ መሆናቸውን አብራርተዋል።

በዚህም በ2017 በጀት አመት 14 ቢሊየን ብር ዋጋ ያላቸው የህክምና መሳሪያዎች በግዢ ወደመጋዘን መግባታቸውን ገልፀዋል።

በተመሳሳይ 17 ቢሊየን ብር የሚገመት የወባና ማህፀን በር ጫፍ ካንሰር ክትባትና ሌሎች የጤና ፕሮግራም መድኃኒት መሰራጨቱን ተናግረዋል።

በማዕከላዊ መጋዘን 83 በመቶ የመድኃኒት ክምችት መኖሩን ጠቁመው ፥25 በመቶ ስርጭት በአዲስ አበባ የሚደረግ መሆኑንም አስረድተዋል።

ግጭት ባለባቸው አካባቢዎች ስምንት ቢሊየን ብር ዋጋ ያላቸው መድኃኒቶች መሰራጨታቸውንም ነው የገለፁት።

ተቋሙ የተለያዩ የሪፎርም ስራዎችን እያከናወነ ሲሆን የአዋጆች ማሻሻያና አሰራር የማዘመን ስራዎች ተከናውነዋል ብለዋል።

ተቋሙ ካሉት 63 መጋዘኖች በአምስቱ ላይ ካይዘን በመተግበር ከሶስት ሚሊየን የአሜሪካን ዶላር በላይ ማዳን መቻሉን ተናግረዋል።

በቀጣይም ተቋሙ የሚያከናውነውን የማሻሻያ ስራ በማጠናከር የተሻለ አገልግሎት ለመስጠት እንደሚሰራ ጠቁመዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም