ምክር ቤቱ ሁለት የብድር ስምምነቶችን አፀደቀ - ኢዜአ አማርኛ
ምክር ቤቱ ሁለት የብድር ስምምነቶችን አፀደቀ
አዲስ አበባ፤ ጥር 19/2017(ኢዜአ)፦ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ዛሬ ባካሄደው አንደኛ ልዩ ስብሰባ መንግስት ከዓለም አቀፉ የልማት ማህበር ጋር ያደረጋቸውን ሁለት የብድር ስምምነቶችን አፅድቋል።
የብድር ስምምነቶቹ የፋይናንስ ዘርፉን ለማጠናከርና የመንግስት አገልግሎትን ለማሻሻል የሚውሉ ናቸው ተብሏል።
የብድር ስምምነቶቹን አስመልክቶ የገንዘብ ሚኒስትር ዴኤታ እዮብ ተካልኝ (ዶ/ር) ለምክር ቤቱ ማብራሪያ ሰጥተዋል።
ኢትዮጵያ ከዓለም አቀፉ የልማት ማህበር ጋር ያደረገችው የ700 ሚሊዮን ዶላር የብድር ስምምነት የፋይናንስ ዘርፉን ጤናማነትና ተወዳዳሪነት የበለጠ ለማሻሻል ያስችላል ብለዋል።
የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያው የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የካፒታል አቅምን እንደሚያሳድግ ገልፀው፤ ብድሩ የኢትዮጵያ ልማት ባንክን አሰራር ለማዘመን ያስችላልም ነው ያሉት።
ኢትዮጵያ ባለፉት አራት ዓመታት የዕዳ ጫናዋ እየቀነሰ መምጣቱንም ነው የተናገሩት።
ኢትዮጵያና ዓለም አቀፉ የልማት ማህበር ለዘመናዊ የመንግስት አገልግሎት ማሻሻያ ፕሮጀክት ማስፈፀሚያ የሚውል የ70 ሚሊዮን ዶላር የብድር ስምምነትም ለምክር ቤተ ቀርቧል።
ምክር ቤቱ በብድር ስምምነቶቹ ላይ ከተወያየ በኃላ ስምምነቶቹን በአብላጫ ድምጽ አፅድቋል።
