ዩኒቨርሲቲው የአካባቢውን እምቅ የተፈጥሮ አቅሞች በጥናትና ምርምር ስራዎች እንዲያጠናክር ድጋፍ ይደረጋል - ኢዜአ አማርኛ
ዩኒቨርሲቲው የአካባቢውን እምቅ የተፈጥሮ አቅሞች በጥናትና ምርምር ስራዎች እንዲያጠናክር ድጋፍ ይደረጋል
መቱ፥ጥር 19/2017 (ኢዜአ)፦መቱ ዩኒቨርሲቲ የአካባቢውን እምቅ የተፈጥሮ አቅም ያማከለ የጥናትና ምርምር ስራዎች እንዲያጠናክር ድጋፍ እንደሚደረግ የዩኒቨርሲቲው የስራ አመራር ቦርድ ሰብሳቢ ብሩክ ታዬ (ዶ/ር) አስታወቁ።
የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ሆልዲንግስ ዋና ስራ አስፈጻሚና የመቱ ዩኒቨርሲቲ የሥራ አመራር ቦርድ ሰብሳቢ ብሩክ ታዬ (ዶ/ር) እና ሌሎች የስራ ሃላፊዎች የዩኒቨርሲቲውን የስራ እንቅስቃሴ ተዘዋውረው ተመልክተዋል።
የሥራ አመራር ቦርድ ሰብሳቢው፥ ዩኒቨርሲቲው ያለበት የኢሉአባቦር ዞንና አካባቢው ትልቅ የመልማት አቅም ያለው የተፈጥሮ ሀብት የታደለ መሆኑን ተናግረዋል።
እነዚህ የተፈጥሮ ሀብቶች በአግባቡ ለምተው የአካባቢውን ማህብረሰብ እና የአገርን ልማት መደገፍ እንዲችሉ ዩኒቨርሲቲው ማገዝ እንዳለበትም አመልክተዋል።
በተጨማሪም ዩኒቨርሲቲዎች ትልቅ የሀገር አቅም የሚፈጠርባቸው ቦታዎች እንደመሆናቸው፥ መቱ ዩኒቨርሲቲም በዚህ ረገድ ውጤታማ ስራ እንዲያከናውን የስራ አመራር ቦርዱ አስፈላጊውን ድጋፍ ያደርግለታል ብለዋል።
ለዚህ ደግሞ ሁሉም የዩኒቨርስቲው ምሁራንና የአመራር ቁርጠኝነት ወሳኝ መሆኑን ነው ያመለከቱት።
የመቱ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ዓለሙ ዲሳሳ (ዶ/ር) በበኩላቸው፥ ዩኒቨርሲቲው ከመማር ማስተማር ሥራው በተጓዳኝ በጥናትና ምርምር እንዲሁም በማሕበረሰብ አገልግሎት በርካታ ስራዎች እያከናወነ ነው።
በተለይም ዩኒቨርሲቲው በአካባቢው ማኅበረሰብ በግብርና ዘርፍ ምርታማነት እንዲጎለብት ውጤታማ የጥናትና ምርምር ስራዎች በማከናወን ላይ መሆኑን ተናግረዋል።
በዚህም የተሻሻሉ የአትክልት፣የፍራፍሬ እና የእንስሳት ዝርያዎች ለአካባቢው አርሶ አደሮች ማቅረብ የሚያስችሉ የምርምር ስራዎች መሰራታቸውን አስታውቀዋል።