ቀጥታ፡

ጥምረቱ የህክምና አገልግሎት አሰጣጥን ለማሻሻል እያጋዘን ነው-የተለያዩ ሆስፒታሎች

አዳማ፤ጥር 19/2017(ኢዜአ)፦የጤና ሚኒስቴር የሚተገብረው ”የኢትዮጵያ ሆስፒታሎች ጥምረት ለጥራት” የህክምና አገልግሎት አሰጣጥን ለማሻሻል እያጋዘቸው መሆኑን ኢዜአ ያነጋገራቸው ሆስፒታሎች ገለጹ።

ኢዜአ የንግሥት እሌኒ፣ የቢሾፍቱና የጋምቤላ ሆስፒታሎች ሃላፊዎችን ያነጋገረ ሲሆን ጥምረቱ የአገልግሎት አሰጣጣቸው እንዲሻሻል እያገዛቸው ነው።

ጥምረቱ የሆስፒታሎችን አቅም ከመገንባት ባለፈ የማህበረሰቡን የጤና አገልግሎት ፍላጎት ለማሻሻልና የአገልግሎት አሰጣጥ ጥራትን ለማሳደግ እያገዘ መሆኑንም ገልጸዋል።

በዋቸሞ ዩኒቨርሰቲ የንግሥት እሌኒ ኮምፕሬሄንሲቪ እስፔሻላይዝድ ሆስፒታል ተወካይ ዶክተር ወንድሙ አሰፋ፤ ጥምረቱ ከአቻ ሆስፒታሎች ጋር የእርስ በእርስ ግንኙነት በመፍጠር የተሻለ የህክምና አገልግሎት ለህብረተሰቡ እንድንሰጥ እድል ፈጥሯል።

በተለይ የጨቅላ ህፃናት ህክምና፣ የቀዶ ህክምና፣ ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎች ህክምናና ክትትል፣ የድንገተኛና ፅኑ ህሙማን ህክምና አገልግሎት እንዲሻሻልና እንዲሳለጥ ማገዙን አስረድተዋል።


 

በዚህም ጥምረቱ የተሻለ ልምድና ተሞክሮ በመለዋወጥ በህክምና አገልግሎቱ የተሻለ ለውጥ እንዲመጣ ገንቢ ሚና እያበረከተ ይገኛል ብለዋል።

የተገኘውን ልምድና ተሞክሮ በመቀመርም በስራችን ያሉ የመጀመሪያ ደረጃ ሆስፒታሎችና ጤና ጣቢያዎች የቴክኒክ ድጋፍ በመስጠት አሰራራቸው እንዲሻሻል እየሰራን ነው ብለዋል።

የቢሾፍቱ አጠቃላይ ሆስፒታል ሥራ እስኪያጅ ዶክተር ታደሰ ጎፋ በበኩላቸው፥ የሆስፒታሎች ጥምረት ለጥራት የተሻለ የጤና አገልግሎት ተደራሽ እንዲሆን ምቹ መደላድል ፈጥሯል ነው ያሉት።

እንደ እ.ኤ.አ በ2012 የተጀመረው የኢትዮጵያ ሆስፒታሎች ጥምረት ለጥራት በሆስፒታሉ የህክምና አገልግሎቶች ጥራትን በማሻሻል የተገልጋይ እርካታ አምጥቷል ብለዋል።


 

ጥምረቱ የሆስፒታሉን የውስጥ ገቢ በማሳደግ እና አስተዳደራዊ መዋቅርን በማጠናከር ረገድ አመርቂ ተግባር ለማከናወን ማስቻሉን አስረድተዋል።

ሌሎች ሆስፒታሎች የውስጥ ችግሮቻቸውን ለመፍታት የተጠቀሙት አዳዲስ አሰራሮች፣ የለውጥ ሀሳቦች እንዲሁም ምርጥ ተሞክሮዎች በመውሰድና በመተግበር የተሻለ አገልግሎት በመስጠት ላይ እንደሚገኙም ተናግረዋል።

የቢሾፍቱ ሆስፒታል በአሁኑ ወቅት በአማካይ በቀን እስከ 1 ሺህ 500 በዓመት ደግሞ 300 ሺህ ህሙማን አገልግሎት እየሰጠ እንደሚገኝ ከሥራ አስኪያጁ ገለፃ ለመረዳት ተችሏል።

የጋምቤላ የመጀመሪያ ደረጃ ሆስፒታል ሥራ አስኪያጅ አቶ ሮን ጎኝ፤ የሆስፒታሎች ጥምረት የሆስፒታሉ ህክምና አገልግሎት አሰጣጥ ያለበት ነባራዊ ቁመና ለማወቅ ያስቻለ ነው ብለዋል።

ጥምረቱ ከሌሎች ጠንካራ ሆስፒታሎች ምርጥ ተሞክሮ በመውሰድ እና በመተግበር በህክምና አገልግሎት ተጨባጭ ውጤት ማስገኘቱን ተናግረዋል።


 

በተለይ በሆስፒታሉ ውስጥ የነበረውን የግብዓት አጠቃቀም፣ የሰው ሃይል፣ የመድኃኒት አቅርቦት ችግር በመቀነስ በኩል ገንቢ ሚና መጫወቱን አስረድተዋል።

በጤና ተቋማት መካከል ጥምረትን በመፍጠር፣ የመረጃ ልውውጥንና መማማርን በማመቻቸት በኩል ዓይነተኛ መሳሪያ ሆኖ እያገለገለን ነው ሲሉ አቶ ሮን አብራርተዋል።

ሰሞኑን በአዳማ ከተማ ”የኢትዮጵያ ሆስፒታሎች ጥምረት ለጥራት” እንቅስቃሴ ላይ ያተኮረ ውይይት ተካሄዷል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም