ቀጥታ፡

ፕሬዝዳንት ታዬ አጽቀ ሥላሴ ናይሮቢ ገቡ

አዲስ አበባ፤ ጥር 18/2017 (ኢዜአ)፦ ፕሬዝዳንት ታዬ አጽቀ ሥላሴ በአፍሪካ ህብረት ተቋማዊ ማሻሻያ የከፍተኛ ደረጃ ስብሰባ ላይ ለመሳተፍ ዛሬ ኬንያ ናይሮቢ ገብተዋል።

ፕሬዚዳንት ታዬ ጆሞ ኬንያታ ዓለም አቀፍ አየር ማረፊያ ሲደርሱ የኬንያ የኢንቨስትመንት፣ ንግድ እና ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር ዋና ፀሐፊ ሊ ኪንያንጁ፣ በኬንያ የኢትዮጵያ ኤምባሲ ምክትል ሚሲዮን መሪ አምባሳደር ደመቀ  አጥናፉ እና ሌሎች የኤምባሲው ዲፕሎማቶች አቀባባል አድርገውላቸዋል።

በኬንያ ፕሬዝዳንት ዊሊያም ሩቶ የሚመራው ስብሰባ ነገ እና ከነገ በስቲያ ይካሄዳል። 

ስብሰባው በአፍሪካ ህብረት ተቋማዊ ማሻሻያ በተለይም በህብረቱ ዘላቂ ፋይናንስ እና የስራ መዋቅር ማሻሻያ እንዲሁም ህብረቱ ለአህጉራዊ ፈተናዎች መፍትሄ በመስጠት ግቦቹን ማሳካት የሚችልበት አቅም መገንባት ላይ ያተኮረ መሆኑን በኬንያ የኢትዮጵያ ኤምባሲ መረጃ ያመለክታል።

የአፍሪካ ሀገራት መሪዎች እና ፖሊሲ አውጪዎች በስብሰባው ላይ ይሳተፋሉ።

ዊሊያም ሩቶ እ.አ.አ በየካቲት ወር 2024 የአፍሪካ ህብረት የተቋማዊ ማሻሻያ ስራ እንዲመሩ መመረጣቸው የሚታወስ ነው።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም