ቀጥታ፡

የስጋ ደዌ በሽታን እንደ ሀገር ሙሉ በሙሉ ለማጥፋት የተቀናጀ ጥረት ይጠይቃል- ሚኒስቴሩ

አዲስ አበባ፤ ጥር 18/2017(ኢዜአ)፦ በኢትዮጵያ የስጋ ደዌ በሽታን ሙሉ በሙሉ ለማጥፋት ሁሉም ባለድርሻ አካላት የነቃ ተሳትፎ እንዲያደርጉ ጤና ሚኒስቴር ጠየቀ።

የዓለም የስጋ ደዌ ቀን በዓለም አቀፍ ደረጃ ለ71ኛ ጊዜ በኢትዮጵያ ደግሞ ለ26ኛ ጊዜ ''የሥጋ ደዌ በሽታን አንዘንጋ'' በሚል መሪ ሀሳብ በአዲስ አበባ ተከብሯል።

በጤና ሚኒስቴር የበሽታ መቆጣጠርና መከላከል መሪ ሥራ አስፈፃሚ ዶክተር ህይወት ሠለሞን እንዳሉት፤ የስጋ ደዌ በሽታን ለማጥፋት በተከናወኑ ተግባራት ተጨባጭ ለውጦች ተመዝግበዋል።

በ1979 ዓ.ም በበሽታው ከተያዙ ሰዎች መካከል 70 በመቶው የአካል ጉዳት ይደርስባቸው እንደነበር አውስተው፤ በ2016 ዓ.ም ቁጥሩን ወደ ዘጠኝ በመቶ ማውረድ መቻሉን ለአብነት አንስተዋል።

በተለይም በሕፃናት ላይ በስጋ ደዌ ምክንያት የሚከሰትን የአካል ጉዳት መጠን ለመቀነስ በተሰሩ ስራዎች ለውጥ መምጣቱን ነው የተናገሩት።

የበሽታው ስርጭት ቢቀንስም የስጋ ደዌ ተጠቂዎችን የማግለል ሁኔታ አሁንም ያልተሻገርነው ችግር ነው ብለዋል።

በአሁኑ ወቅት በተለይም በሕፃናት ላይ የስጋ ደዌ በሽታ እንዳይታይ የሁሉም አካላት ርብርብ ያስፈልጋል ነው ያሉት።

በሽታውን ለመቀነስ የተከናወኑ ተግባራት ውጤት ቢያመጡም ሙሉ ለሙሉ ከሀገሪቱ ለማጥፋት ቀሪ የቤት ስራዎች መኖራቸውን ነው የጠቆሙት።

የሴቶችና ማሕበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ ወይዘሮ ሁሪያ አሊ በበኩላቸው፤ መንግስት በአሁኑ ወቅት የአካል ጉዳተኞችን መብት ለማስከበር አካታች የሆኑ ተግባራትን እያከናወነ ነው ብለዋል።

በጤናው ዘርፍ ከተከናወኑ ተግባራት መካከልም የስጋ ደዌ ተጠቂዎች የሚደርስባቸውን የአካል ጉዳት ከመቀነስ አንፃር ውጤት እየታየ መሆኑን አንስተዋል።

ውጤቱ ቀጣይነት እንዲኖረውም የበሽታው ተጠቂዎችን የመንከባከብ፣ የመደገፍና አቅማቸውን የማጎልበት ተግባር ርብርብ እንደሚያስፈልገው ጠቁመዋል።

የኢትዮጵያ የሥጋደዌ ተጠቂዎች ብሔራዊ ማሕበር ሊቀመንበር አቶ ከፍያለው በቀለ በበኩላቸው፤ የስጋ ደዌ ተጠቂዎችን ለማከም፣ ለመደገፍና ለመንከባከብ የተደረገው የጋራ ጥረት ውጤት አምጥቷል ብለዋል።

በዘርፉ የተገኝው ውጤት በጋራ ጥረት የመጣ ቢሆንም መዘናጋት እንዳይኖር አሁንም በቅንጅት መስራት አስፈላጊ እንደሆነ አሳስበዋል።

የኢትዮጵያ አካል ጉዳተኞች ማበራት ፌዴሬሽን ፕሬዚዳንት አቶ አባይነህ ጉጆ በበኩላቸው፤ ማሕበሩ በበርካታ ውጣ ውረዶች አልፎ የአባላቱን ፍላጎት ለማሟላት ሰፊ ጥረት እያደረገ መሆኑን ተናግረዋል።

በተለይም የስጋ ደዌ ሕሙማን ከሌሎች አካል ጉዳተኞች በተለየ መልኩ የሚደርስባቸውን መገለል ለማስቀረት አሁንም ብዙ ርቀት መሔድ እንደሚያስፈልግ አንስተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም