ቀጥታ፡

በዱባዩ የልዩ መሳሪያዎችና ታክቲኮች(ስዋት) ዓመታዊ ውድድር የሚሳተፍ የፖሊስ ቡድን ሽኝት ተደረገለት

አዲስ አበባ፤ ጥር 18/2017(ኢዜአ)፦ በዱባይ የ2025 የልዩ መሳሪያዎች እና ታክቲኮች ዓለም አቀፍ ውድድር(ስዋት) የሚሳተፍ የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ ቡድን ወደ ዱባይ አቅንቷል።

የፌዴራል ፖሊስ (ስዋት) ቡድኑ የተባበሩት ዐረብ ኢምሬትስ በየዓመቱ በምታዘጋጀው ዓለም አቀፍ የሕግ አስከባሪ ቡድኖች ውድድር ላይ ለመሳተፍ ነው ወደ ዱባይ ያቀናው።

በፈረንጆቹ የካቲት 1 ቀን 2025 በሚደረገው በዚህ ውድድር የሚሳተፈው የስዋት ቡድኑ በቂ ዝግጅት ማድረጉን ተገልጿል።

የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ ኮሚሽነር ጀነራል ደመላሽ ገብረ ሚካኤል ለስዋት ብድኑን ሽኝት አድርገዋል።

ኮሚሽነር ጀነራል ደመላሽ ገብረ ሚካኤል ቡድኑ ተወዳድሮ ከማሸነፍ ባለፈ በፈጣን ምላሽ ሰጭነት ላይ ተሞክሮውን ለማካፈል፣ ከዓለም አቀፍ ልምምዶች ጋር ለመተዋወቅ፣ ከተለያዩ ሀገራት ጥሩ ተሞክሮዎችን ለመቅሰም እና ዝግጁነቱን የበለጠ ለማሳደግ ውድድሩ ጠቀሜታ እንዳለው ገልፀዋል።

ለተወዳደሪ የስዋት ቡድን አባላቱ በውድድሩ ላይ መልካም ፖሊሳዊ ሥነ-ምግባር በማሳየት በብቃት ተወዳድራችሁ ባሸናፊነት የሀገራችንን እና የተቋማችንን መልካም ገጽታ በዓለም መድረክ ላይ እንድታስተዋውቁ በማለት የሥራ መመሪያ ሰጥተዋል።

ቡድኑ በታክቲካል ኦፕሬሽን፣ በጥቃት መመከት፣ በቪአይፒ አመራር የማዳን ተልዕኮ፣ በከፍተኛ ታወር መውጣትና መውረድ እንዲሁም በመሰናክል ኮርስ ዘርፎችን እንደሚወዳደር ታውቋል።

በውድድሩም አሜሪካና ቻይናን ጨምሮ ከ50 ሀገራት የተውጣጡ ከ120 በላይ የስዋት ቡድኖች እንደሚሳተፉ የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ መረጃ ያመለክታል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም