ቀጥታ፡

የዜጎችን አገልግሎት አሰጣጥ የማዘመንና ስራ ተጠናክሮ ይቀጥላል - ኢንጂነር ወንድሙ ሴታ

አዲስ አበባ፤ ጥር 18/2017(ኢዜአ)፦ የዜጎችን አገልግሎት አሰጣጥ ይበልጥ የማዘመንና ተደራሽ የማድረግ ስራ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል በምክትል ከንቲባ ማዕረግ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ዋና ስራ አስኪያጅ ኢንጂነር ወንድሙ ሴታ ገለጹ።

የሲቪል ምዝገባና የነዋሪነት አገልግሎት ኤጀንሲ መደበኛ የሰራተኛ የደንብ ልብስ የማልበስ ስነ-ስርዓትና ሁለተኛውን የእውቅና መርሃ ግብር አካሒዷል፡፡

በመርሃ-ግብሩ ላይ ንጂነር ወንድሙ ሴታን ጨምሮ የከተማ አስተዳደሩ የስራ ሃላፊዎችና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ተገኝተዋል፡፡

በዚህም ከማዕከል እስከ ወረዳ የሚሰሩና የላቀ አፈጻጸም ያስመዘገቡ የተቋሙ አመራሮችና ሰራተኞች እውቅና እና ሽልማት ተበርክቶላቸዋል፡፡

ኢንጂነር ወንድሙ ሴታ በዚሁ ወቅት የሲቪል ምዝገባና የነዋሪነት አገልግሎት ኤጀንሲ የሪፎርም ስራ በስፋት እየተሰራባቸው ካሉ ተቋማት መካከል አንዱ መሆኑን ገልጸዋል፡፡


 

ከሪፎርሙቹ መካከልም የአሰራር ስርዓቶችን በቴክኖሎጂ መደገፍ፣ የአደረጃጀት፣ የሰው ሃብት ልማትና ምቹ የስራ አካባቢ መፍጠር እንደሚገኙበትም ተናግረዋል።

በዚህም ባለፉት የለውጥ አመታት አመርቂ ውጤቶች መመዝገባቸውን ነው የገለጹት፡፡

ኤጀንሲው ከዚህ በፊት በርካታ የመልካም አስተዳደር ችግሮች ይነሱበት እንደነበር ጠቅሰው፤ በአሁኑ ወቅት ግን ዜጎች ያለምንም እንግልት አገልግሎት እያገኙ መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡


 

በቀጣይም የዜጎችን አገልግሎት አሰጣጥ የማሻሻል፣ የማዘመንና ይበልጥ ተደራሽ የማድረግ ተግባር ተጠናክሮ እንደሚቀጥል አረጋግጠዋል፡፡

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ሲቪል ምዝገባና የነዋሪነት አገልግሎት ኤጀንሲ ዋና ዳይሬክተር ዮናስ አለማየሁ በበኩላቸው፤ ኤጀንሲው ባለፉት አመታት የሚሰጠውን አገልግሎቶች ለማሻሻል በርካታ የሪገፎርም ስራዎችን ሲያከናውን መቆየቱን ተናግረዋል።

በዛሬው እለትም የተከናወነው የሲቪል ምዝገባና የነዋሪነት አገልግሎት ኤጀንሲ መደበኛ የሰራተኛ የደንብ ልብስ እንዲለብሱ መደረጉ የሪፎርሙ አካል መሆኑን ገልጸዋል።

ካለፉት ሁለት አመታት ተኩል ወዲህም በዜጎች አገልግሎት አሰጣጥ ላይ ከፍተኛ መሻሻል ማስመዝገብ መቻሉን ገልጸዋል።

ዛሬ የተሰጠን እውቅና በቀጣይ ስራችንን የበለጠ እንድናከናውን የሚያስችል ነው ያሉት ደግሞ ከተሸላሚዎች መካከል ዘነበች ጌታነህ እና ውሬህይወት በላይነህ ናቸው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም