ቀጥታ፡

ስፖርትና ዕውቀትን በማቀናጀት በትምህርት ጥራት ላይ የተጀመሩ ስራዎችን ማጠናከር ይገባል- ሚኒስትሩ ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ

አዲስ አበባ፤ ጥር 18/2017(ኢዜአ)፦ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ስፖርትና ዕውቀትን በማቀናጀት በትምህርት ጥራት ላይ የተጀመሩ ስራዎችን በማጠናከር ለሀገር ዕድገት ከፍ እንዲጎለብቱ የትምህርት ሚኒስትሩ ፕሮፌሰር ብርሀኑ ነጋ አሳሰቡ።

የዩኒቨርስቲ ተማሪዎች ስፖርት ፌስቲቫል በአዲስ አበባ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ ተከፍቷል።

የትምህርት ሚኒስትሩ ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ በፌስቲቫሉ መክፈቻ ላይ እንዳሉት ስፖርትና እውቀትን ከትምህርት ጥራት ስራዎች ጋር በማስተሳሰር የአገርን ዕድገት ከፍ ማድረግ ይገባል፡፡

የአዕምሮና የአካል ዕድገት የተሳሰሩ መሆናቸውን የጠቆሙት ሚኒስትሩ ተወዳዳሪዎች በቆይታቸው ሰላምን፤ ወዳጅነትና አብሮነትን በማስቀደም የስፖርት ፌስቲቫሎችን ማካሄድ እንደሚጠበቅባቸውም ተናግረዋል።

ከቀጣይ የትምህት ዘመን ጀምሮ ዩኒቨርስቲዎችን ጨምሮ በአገር ውስጥ ያሉ ትምህርት ቤቶች በሙሉ አዲስ የሊግ ወድድሮች እንደሚያካሄዱ ሚኒስትሩ ጠቁመዋል፡፡

በአጠቃላይ ትምህርት ዘርፍ ከመጀመሪያ እስከ ሁለተኛ ደረጃ ያሉ ትምህርት ቤቶች በሊግ ተደራጅተው ከወዲሁ ውድድሮችን በማካሄድ ላይ መሆናቸውንም አመልክተዋል።

የባህልና ስፖርት ሚኒስትር ዴኤታ መኪዩ መሐመድ በበኩላቸው የዩኒቨርስቲዎች ስፖርት ፌስቲቫል በዩኒቨርስቲዎች ውስጥ ስፖርት ማዘውተሪያዎች እንዲስፋፉ፣ በዩኒቨርስቲዎችና በተማሪዎች መካከል መልካም ግንኙነት እንዲፈጠር፣ የስፖርት ተሳትፎ እንዲጎለብትና ምቹ መማማር ማስተማር ከባቢ እንዲፈጠር እንደሚያስችል ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ዩኒቨርስቲዎች ስፖርት ማህበር ፕሬዚዳንት አቶ አባይ በላይሁን በበኩላቸው ውድድሩ በኮቪድና በተለያዩ ምክንያቶች ለዘጠኝ አመታት ተቋርጦ የቆየውን ውድድር ትምህርት ሚኒስቴር ዩኒቨርስቲዎች ተቀራራቢ ካላንደር እንዲኖራቸው በማድረጉ ዕውን ሊሆን መቻሉን ጠቅሰዋል፡፡

የውድድሩ አዘጋጅ የአዲስ አበባ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርስቲ ፕሬዚዳንት ዶክተር ደረጀ እንግዳ በዚሁ ጊዜ ሲናገሩ ስፖርት ለአንድነትና ለእድገት በሚል መሪ ቃል የሚካሄደውን ይህን የስፖርት ፌስቲቫል ቀጣይነት ለማረጋገጥ ዩኒቨርስቲው በአጭር ጊዜ ወስጥ ውድድሩን ማዘጋጀቱን ገልጸዋል።

ከጥር 17 – 27/ 2017 ዓ.ም በሚካሄደው በዚህ ውድድር በአምስት ስፖርት አይነቶች ከ49 ዩኒቨርስቲዎች የተውጣቱ 2500 ስፖርተኞች እንደሚሳተፉ ከትምህርት ሚኒስቴር የተገኘው መረጃ ያመለክታል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም