ቀጥታ፡

ኢዜአ የኢትዮጵያን እውነት፣ ታሪክና ትርክት ለዓለም በሚገባ ለማሳወቅ በሚያደርገው ጥረት አስፈላጊው ድጋፍ ይደረጋል - አቶ አደም ፋራህ

አዲስ አበባ፤ ጥር 17/2017(ኢዜአ)፡- ኢዜአ የኢትዮጵያን እውነት፣ ታሪክና ትርክት ለዓለም በሚገባ ለማሳወቅ በሚያደርገው ጥረት አስፈላጊው ድጋፍ እንደሚደረግ በምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ማዕረግ የዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታ ማስተባበሪያ ማዕከል ኃላፊና የብልጽግና ፓርቲ ምክትል ፕሬዝዳንት አደም ፋራህ ገለጹ።

በምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ማዕረግ የዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታ ማስተባበሪያ ማዕከል ኃላፊና የብልጽግና ፓርቲ ምክትል ፕሬዝዳንት አደም ፋራህ፣ የፕላንና ልማት ሚኒስትር ፍጹም አሰፋ(ዶ/ር)፣ የብልጽግና ፓርቲ የህዝብና ዓለም አቀፍ ግንኙነት ዘርፍ ኃላፊና የኢዜአ የስራ አመራር ቦርድ ሰብሳቢ ቢቂላ ሁሪሳ(ዶ/ር) እና ሌሎች የመንግስት የስራ ኃላፊዎች ኢዜአን ጎብኝተዋል።


 

አቶ አደም ፋራህ በዚሁ ጊዜ እንደገለጹት ኢዜአ ተልእኮውን ለመወጣት እያከናወነ ያለው የሪፎርም ስራ የሚበረታታ ነው ብለዋል።

ተቋሙ በአደረጃጀት እንዲሁም በሚዲያ ቴክኖሎጂ ልማት እያከናወናቸው ያሉ ተግባራት በአርአያነት የሚጠቀሱ መሆናቸውን አንስተዋል።

እውነትና መርህ በሚፈተኑበት በዚህ የድህረ እውነት ዘመን የኢትዮጵያን ብሎም የአፍሪካን እውነት ለማሳወቅ የሚሰሩ እንደ ኢዜአ ያሉ ተቋማት ሚናቸው የጎላ መሆኑን ተናግረዋል።


 

ኢዜአ በተለይ ብሄራዊ መግባባት በመፍጠር፣ ብሄራዊ ጥቅምን በማስጠበቅና ሀገራዊ አንድነትን በማጠናከር ረገድ ትልቅ አስተዋጽኦ እያበረከተ መሆኑን ገልጸዋል።

የህዝቦች ትስስር እንዲጠናከርና ሀገራዊ አንድነት እንዲጎለብት ትልቅ አስተዋጽኦ እያበረከተ እንደሚገኝም ነው የተናገሩት።

የኢትዮጵያ ድምጽ በመሆን እውነቷን፣ ታሪኳንና ትርክቷን ለዓለም ለማስተዋወቅ እያደረገ ያለውን ጥረት አጠናክሮ መቀጠል አለበት ብለዋል።

ተልእኮውን በበለጠ ብቃት ለመወጣት ቀጣይነት ያለው የሰው ኃይል ግንባታ ላይ በትኩረት ሊሰራ እንደሚገባም ገልጸዋል።


 

የኢትዮጵያን ራዕይና ስኬቶች በማስተዋወቅ፣ እንደ ሀገር የገጠሙ ፈተናዎችን ለመሻገር የተኬደበትን ርቀት እንዲሁም የተመዘገቡ ውጤቶችን ለዓለም በመግለጽ ረገድ በበለጠ ትኩረት መስራት ይገባዋል ነው ያሉት።

ኢዜአ የኢትዮጵያ ብሎም የአፍሪካ ድምጽ በመሆን ጎልቶ ለመውጣት በሚያደርገው ጥረት ሁሉ አስፈላጊው ድጋፍ እንደሚደረግም አቶ አደም ፋራህ አረጋግጠዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም