ቀጥታ፡

በከተማ ልማት ስራዎቻችን ሁለንተናዊ እመርታን ለማረጋገጥ የሚያስችሉ መደላድሎች ተፈጥረዋል - አሕመዲን መሐመድ(ዶ/ር)

አዲስ አበባ፤ ጥር 17/2017(ኢዜአ)፡- በከተማ ልማት ስራዎቻችን ሁለንተናዊ እመርታን ለማረጋገጥ የሚያስችሉ መደላድሎች ተፈጥረዋል ሲሉ በምክትል ርዕሰ መሥተዳድር ማዕረግ የከተማ ዘርፍ አስተባባሪና የከተማ እና መሠረተ ልማት ቢሮ ኃላፊ አሕመዲን መሐመድ(ዶ/ር) ገለጹ።


 

በዛሬው ዕለት የክልላችን የከተማ ልማት ክላስተር ተቋማትን የ2017 በጀት ዓመት የመጀመሪያ ግማሽ ዓመት የስራ አፈጻፀም ገምግመናል ሲሉ አሕመዲን መሐመድ(ዶ/ር) በማህበራዊ ትስስር ገጻቸው ባሰፈሩት መልዕክት ገልጸዋል።

ቀድሞ የነበሩ ግብረመልሶችን ታሳቢ በማድረግ የሰው ኃይል ግንባታ፣ አሰራር ማዕቀፍ፣ ቴክኖሎጂ፣ ግብዓቶች እና ምቹ ሁኔታ መፍጠር ከውጤታማነት አኳያ በሁሉም ተቋማት ቀርበዋል ብለዋል።

መልካም አስተዳደር፣ ስራ ዕድል ፈጠራ፣ ኑሮ ውድነት፣ ገቢ አሰባሰብ፣ ኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ፣ ካዳስተር፣ ቱሪዝም፣ ትራንስፖርት፣ ስማርት ሲቲ፣ ኮሪደር ልማት፣ መሬት አስተዳደር እና ሌሎች የትኩረት መስኮች ላይ ውጤቶች መመዝገባቸውን አይተናል ሲሉም ገልጸዋል።


 

መልካም ውጤቶችን የማላቅ እና የተስተዋሉ ጉድለቶችን በቀሪ ወራት በሚተገበሩበት አካሄድ ላይ ተግባብተናል ብለዋል በመልዕክታቸው።

በተመረጡ ተግባራት የጋራ ዕቅድ በማዘጋጀትና እስከ ታችኛው መዋቅር በማውረድ፤ ጠንካራ ክትትልና ድጋፍ በማድረግ ቀጣይ ስራዎችን በቅንጅትና ትብብር የምንመራ ይሆናል ብለዋል።

እየተሻሻለ ለመጣው የተቋም ግንባታ ሂደት እና ለተመዘገቡ ውጤቶች በየደረጃው ለሚገኘው አመራርና ባለሙያ እንዲሁም ተገልጋዮችና ደንበኞች ምስጋና አቅርበዋል አሕመዲን መሐመድ(ዶ/ር) በመልዕክታቸው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም