ቀጥታ፡

በክልሉ ብቁና ተወዳዳሪ ዜጋን ለማፍራት በትምህርት ዘርፍ ሁሉም በቅንጅት መሥራት አለበት - አቶ ጌታቸው ረዳ

መቀሌ፤ጥር 17/2017 (ኢዜአ)፦በትግራይ ክልል ብቁ እና ተወዳዳሪ ዜጋን ለማፍራት መንግስት፣መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች እና መላው ህብረተሰብ በቅንጅት መሥራት እንዳለባቸው የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ፕሬዚዳንት ጌታቸው ረዳ አሳሰቡ።

በክልሉ በተያዘው ዓመት 12 ልዩ አዳሪ ትምህርት ቤቶችን ለመገንባት የሚያስችል የገቢ ማሰባሰቢያ ቴሌቶን በመቀሌ ከተማ እየተካሄደ ነው።

መርሃ ግብሩን በንግግር የከፈቱት የጊዜያዊ አስተዳደሩ ፕሬዚዳንት ጌታቸው ረዳ ፥ በክልሉ ብቁ እና ተወዳዳሪ ዜጋን ለማፍራት መንግስት፣ መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች እና መላው ህብረተሰብ በቅንጅት መሥራት አለባቸው።

የትምህርት ዘርፉን ለማጠናከር ሁሉም የማህበረሰብ ክፍል በገንዘቡ፣ በጉልበቱና በእውቀቱ ድጋፍ እንዲያደርግ ጥሪ አቅርበዋል።

ሁሉም አዳሪ ትምህርት ቤቶችን ለመገንባት የሚያስችለውን ገቢ በትግራይ ልማት ማህበር ጥላ ሥር ተደራጅቶ መደገፍ እንዳለበት ተናግረዋል።

የትልማ ዋና ዳይሬክተር አቶ ተስፋይ ገብረ እግዚአብሄር፥ በበኩላቸው በቴሌቶን ዝግጅቱ ዘንድሮ ለሚገነቡ አዳሪ ትምህርት ቤቶች አንድ ነጥብ ስድስት ቢሊዮን ብር ለመሰብሰብ ታቅዷል።

ዛሬ እየተካሄደ ባለው የገቢ ማሰባሰቢያ ቴሌቶን ላይ የክልሉ መንግስት ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎችና ሌሎች የህብረተሰብ ክፍሎች እየተሳተፉ ነው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም