ቀጥታ፡

ሆስፒታሎችን በማስተሳሰር የህብረተሰቡን የአገልግሎት እርካታ ለማሳደግ ምቹ መደላድል ተፈጥሯል - ዶክተር መቅደስ ዳባ

አዳማ፤ ጥር 17/2017(ኢዜአ)፡- በሆስፒታሎች መካከል ጠንካራ ትስስር በማመቻቸት የህብረተሰቡን የአገልግሎት እርካታ ለማሳደግ ምቹ መደላድል መፈጠሩን የጤና ሚኒስትር ዶክተር መቅደስ ዳባ ገለጹ።

ሚኒስቴሩ ያዘጋጀው “የኢትዮጵያ ሆስፒታሎች ጥምረት ለጥራት” መርሃ ግብር የስድስት ወራት አፈጻጸም የግምገማ መድረክ በአዳማ ከተማ ተካሂዷል።

ለሁለት ቀናት ሲካሄድ የቆየው መድረኩ ዛሬ ሲጠናቀቅ የተገኙት ሚኒስትሯ እንደተናገሩት፤ እንደ ሀገር ጠንካራ የጤና ሥርዓት በመገንባት የአገልግሎት ጥራትን ማረጋገጥ ያስፈልጋል።

ለዚህም “የኢትዮጵያ ሆስፒታሎች ጥምረት ለጥራት” መርሃ ግብር ተቀርፆ በየደረጃው ተግባራዊ እየተደረገ መሆኑን ገልጸዋል።

ይህም በሆስፒታሎች መካከል ጠንካራ ትስስር በመፍጠር የህብረተሰቡን የአገልግሎት እርካታ ለማሳደግ ምቹ መደላድል መሆኑን ተናግረዋል።

በሆስፒታሎች መካከል በመረጃ ላይ የተመሰረተ የህክምና "ሪፈር" ቅብብሎሽን ከማሳለጥ ባለፈ በክረምት ወቅት በርካታ የበጎ ፈቃድ ቀዶ ሕክምና እና ሌሎች የህክምና አገልግሎት በቅንጅት ለህብረተሰቡ ተደራሽ በማድረግ ውጤታማ መሆኑን አውስተዋል።

ሆስፒታሎች የህዝቡን ፍላጎትና እርካታ በተጨባጭ ለማረጋገጥ ብዙ ሥራ መስራት ይጠበቅባቸዋል ያሉት ሚኒስትሯ፤ በዚህ ረገድ ሚኒስቴሩ የህክምና ተደራሽነትንና ጥራትን ለማረጋገጥ የዘርፉን የህክምና ግብዓትና መሠረተ ልማት ለማሟላት እየሰራ መሆኑን ገልጸዋል።

በተለይ በህክምና ተቋማት ከንጽህና ጋር ተያይዞ የሚነሳውን ቅሬታ ለመፍታት ሚኒስቴሩ የጽዱ ጤና ተቋም ኢኒሼቲቭ ቀርፆ ለመተግበር እየሰራ መሆኑን ጠቁመዋል።

የጤና ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር ደረጀ ዱጉማ በበኩላቸው፤ በሀገሪቱ ጠንካራ የጤና ሥርዓት ለመገንባት በሚደረገው እንቅስቃሴ “የኢትዮጵያ ሆስፒታሎች ጥምረት ለጥራት” መርሃ ግብር ጉልህ አስተዋጽኦ እያበረከተ እንደሚገኝ ተናግረዋል።

ሚኒስቴሩ በመርሃ ግብሩ የተገኙ ስኬቶችን አጠናክሮ ለማስቀጠል የቴክኒክና የፋይናንስ ድጋፍ ቀጣይነት እንዲኖረው ይሰራል ብለዋል።

የጤና ተቋማት የንጹህ ውሃ አቅርቦትን ማሻሻል እና ፍሳሽ ቆሻሻ አወጋገድ ላይ ትኩረት ተሰጥቶ ማህበረሰቡን ባሳተፈ መልኩ መሰራት እንዳለበትም አቅጣጫ ተቀምጦ እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል።

በመድረኩ ማጠቃለያ የሁሉም ክልሎች ጤና ቢሮ ኃላፊዎችና ተወካዮች “የኢትዮጵያ ሆስፒታሎች ጥምረት ለጥራት” መርሃ ግብር በቀጣይ በቅንጅት መስራት የሚያስችላቸውን የስምምነት ሰነድ ከሚኒስትሯ ጋር ተፈራርመዋል።

የፌዴራልና የክልል ከፍተኛ አመራር አባላት፣ በየደረጃው የሚገኙ የሆስፒታል የሥራ ኃላፊዎች እና ሌሎች ባለድርሻ አካላት በመድረኩ ተሳትፈዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም