መገናኛ ብዙኃን የኢትዮጵያን ብሔራዊ ጥቅም የሚያስጠብቁ ዘገባዎችን አጠናክረው ሊቀጥሉ ይገባል - ኢዜአ አማርኛ
መገናኛ ብዙኃን የኢትዮጵያን ብሔራዊ ጥቅም የሚያስጠብቁ ዘገባዎችን አጠናክረው ሊቀጥሉ ይገባል
አዲስ አበባ፤ ጥር 17/2017(ኢዜአ)፡- መገናኛ ብዙኃን የኢትዮጵያን ብሔራዊ ጥቅም የሚያስጠብቁ ዘገባዎችን አጠናክረው ሊቀጥሉ እንደሚገባ የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃን ባለስልጣን ገለጸ።
የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃን ባለስልጣን ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ጋር በመተባበር ለመገናኛ ብዙኃን ባለሙያዎች በብሔራዊ ጥቅም፣ በባህል፣ በፖለቲካና በውጪ ጉዳይ ፖሊሲ አዘጋገብ ዙሪያ ስልጠና ሰጥቷል።
የስልጠናው ዋና ዓላማ መገናኛ ብዙሃን እያበረከቱት ያለውን አስተዋጽኦ ይበልጥ ለማጠናከርና አልፎ አልፎ የሚታዩ የአዘጋገብ ክፍተቶችን ለመሙላት ነው ተብሏል።
የባለስልጣኑ ምክትል ዋና ዳይሬክተር ግዛው ተስፋዬ በዚሁ ወቅት፤ መገናኛ ብዙኃን በሀገር ሁለንተናዊ እድገት ውስጥ ጉልህ ሚና እንደሚጫወቱ ገልጸዋል።
ከዚህም ባለፈ ለሀገር ብሄራዊ ጥቅም መከበር፣ ለዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታ፣ ለባህል ዕድገትና ለኢኮኖሚ ሽግግር ሁነኛ መሳሪያ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡
በዚህ ረገድ በኢትዮጵያ የሚገኙ የህዝብም ሆኑ የግል መገናኛ ብዙኃን የሚያሰራጯቸው ዘገባዎች ብሔራዊ ጥቅምን ከማስከበር አኳያ አዎንታዊ ሚና እየተጨወቱ እንደሚገኙ ተናግረዋል፡፡
በቀጣይም ዘገባዎቻቸው የሀገርን ብሔራዊ ጥቅም ይበልጥ የሚያስጠበቁ እንዲሆኑ መስራት አለባቸው ብለዋል።
የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃን ባለስልጣን በአዋጅ በተሰጠው ኃላፊነት መሰረት ለሚዲያዎች አስፈላጊውን ድጋፍና ክትትል እንደሚያደርግም አረጋግጠዋል፡፡
በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የፖለቲካ ሳይንስና ዓለም አቀፍ ግንኙነት መምህር ባዩልኝ ዘመድ አገኘሁ(ዶ/ር) በበኩላቸው፣ ብሔራዊ ጥቅም ከሀገር ህልውና ጋር ቀጥታ ግንኙነት ያለው ነው ብለዋል፡፡
በመሆኑም በሀገሪቱ የሚገኙ መገናኛ ብዙኃን በብሔራዊ ጥቅም ላይ የጋራ አረዳድ በመያዝ ለተግባራዊነቱ አበክረው መስራት እንዳለባቸው አስገንዝበዋል፡፡
እያንዳንዱ ዘገባ የሀገሪቱን ነባራዊ ሁኔታ ያገናዘበ መሆን እንዳለበት የተናገሩት ደግሞ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የፖለቲካ ሳይንስና ዓለም አቀፍ ግንኙነት መምህር ዮናስ አሽኔ(ዶ/ር) ናቸው፡፡
መገናኛ ብዙኃን በመንግስት እና በህዝብ መካከል እንደ አገናኝ ድልድይ ከመሆን ባለፈ የተለያዩ መድረኮችን በማዘጋጀት ብዝኃ ሀሳብን ማንጸባረቅ የሚያስችሉ ሁኔታዎችን ማመቻቸት እንዳለባቸውም ጠቁመዋል።
በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የኢትዮጵያ ጥናት ተቋም ዳይሬክተር ታከለ መርዕድ(ዶ/ር) በበኩላቸው፤ መገናኛ ብዙኃን የኢትዮጵያን ብዝኃ ባህልና ቋንቋ በአግባቡ የሚያስተናግዱ መሆን እንዳለባቸው ተናግረዋል።
በመሆኑም በየትኛውም የፕሮግራም ቅርፅ የሚያሰራጯቸው የይዘት ሥራዎች አካታችና ሚዛናዊ ሊሆኑ ይገባቸዋል ነው ያሉት።
በስልጠናው የተሳተፉ የመገናኛ ብዙኃን ባለሙያዎች በበኩላቸው ከስልጠናው፤ ለሀገር አዎንታዊ አስተዋጽኦ የሚያበረክቱ ዘገባዎችን በተጠናከረ ሁኔታ መስራት የሚያስችል ግንዛቤ ማግኘታቸውን ገልጸዋል፡፡