የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ፈተናዎችን በመቋቋም በተከታታይ ከፍተኛ ዕድገት አስመዝግቧል - ሚኒስትር ፍጹም አሰፋ(ዶ/ር) - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ፈተናዎችን በመቋቋም በተከታታይ ከፍተኛ ዕድገት አስመዝግቧል - ሚኒስትር ፍጹም አሰፋ(ዶ/ር)
አዲስ አበባ፤ ጥር 17/2017(ኢዜአ)፡- ከሀገራዊ ለውጡ ወዲህ የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ፈተናዎችን በመቋቋም በተከታታይ ከፍተኛ ዕድገት ማስመዝገቡን የፕላንና ልማት ሚኒስትር ፍጹም አሰፋ(ዶ/ር) ገለጹ።
ሚኒስትሯ ሀገራዊ የሪፎርም ሥራዎችና የተገኙ ውጤቶችን በተመለከተ ማብራሪያ ሰጥተዋል።
ኢትዮጵያ ባለፉት የለውጥ ዓመታት ሀገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያው ለብዝኃ ዘርፍ የዕድገት ምንጮች ትኩረት ሰጥታ መስራቷን ጠቅሰዋል።
በዓለም አቀፍ ደረጃ ተከስቶ የነበረውን የኮቪድ-19 ወረርሽኝ፣ የአየር ንብረት ለውጥ ተፅዕኖና የጸጥታ ችግሮችን በመቋቋም ኢኮኖሚው ባለፉት አምስት ዓመታት በአማካይ 7 ነጥብ 2 በመቶ ዕድገት ማስመዝገቡን ገልጸዋል።
ይህም ኢትዮጵያን በዓለም በተከታታይ ከፍተኛ ዕድገት ካስመዘገቡ ሀገራት ተርታ አሰልፏታል ነው ያሉት።
ከምስራቅ አፍሪካ አንደኛ፣ ከሰሃራ በታች ሶስተኛ እና ከአፍሪካ አምስተኛ ግዙፍ ኢኮኖሚ መገንባት መቻሉንም ገልጸዋል።
በሀገራዊ ለውጡ የማክሮ ኢኮኖሚ መዛባትን ማስተካከል መቻሉንና በተለይ ደግሞ የመንግስት ገቢ በከፍተኛ ሁኔታ መጨመሩን አንስተዋል።
ከለውጡ በፊት ሀገሪቱ ከፍተኛ የዕዳ ቀንበር ተጭኗት መቆየቱን አንስተው፤ በሀገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያው ምንም ዓይነት የንግድ ብድር ላለመውሰድ ቁርጠኛ አቋም መያዙን ገልጸዋል።
መንግሥት የራስ የልማት አቅምን ለማጠናከር የገቢ አሰባሰቡን ከማጎልበት ባሻገር የተከማቸውን ዕዳ ለመቀነስ ባለፉት አምስት ዓመታት 10 ቢሊዮን ዶላር ብድር ተመላሽ ማድረጉን አንስተዋል።
በዚህም የውጭ የዕዳ ጫና ከሀገራዊ ጥቅል ምርት አንጻር ከለውጡ በፊት የነበረው የ30 በመቶ ምጣኔ አሁን ወደ 13 ነጥብ 7 በመቶ መውረዱን ተናግረዋል።
ሌላኛው ያለፉት የለውጥ ዓመታት ስኬት የውጪ ቀጥተኛ ኢንቨስትመንት መጨመር መሆኑን ጠቅሰው፥ በየዓመቱ በአማካይ ከ3 ቢሊዮን ዶላር በላይ መሳብ መቻሉን ገልጸዋል።
የዘርፎች ዕድገት በተለይም በግብርና የመስኖ ስንዴ፣ የሌማት ትሩፋት፣ የማዕድን፣ የቱሪዝም፣ የአምራች ኢንዱስትሪ ምርታማነት መጨመሩንና የቱሪዝም መሰረተ ልማት መስፋፋቱን አብራርተዋል።
ከዓለም ጋር መወዳደር የሚችል ዘመናዊ ኢኮኖሚ ለመገንባት የተሟላ የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ ከሐምሌ/2016 ዓ.ም ጀምሮ እየተተገበረ እንደሚገኝ ነው ያነሱት።
በማሻሻያው የተሻለ የውጭ ምንዛሬ ፍሰት በኢኮኖሚው ውስጥ እንዲኖር ማስቻሉንና ባለፉት ስድስት ወራት ባንኮች ከሸጡት የውጭ ምንዛሬ የገዙት እንደሚበልጥ ተናግረዋል።
የመበደኛውና የትይዩ ገበያ የምንዛሬ ተመን ልዩነትን በከፍተኛ ሁኔታ በማጥበብ የተረጋጋ ሁኔታ መፈጠሩንም ነው ያስረዱት።
የተሟላ የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያውን ተከትሎ ሊፈጠሩ የሚችሉ ጫናዎችን ለመቋቋም መንግሥት አስፈላጊውን ዝግጅት አድርጎ ወደ ሥራ መግባቱን ጠቅሰዋል።
በዚህም ተለዋዋጭ የዋጋ ሁኔታዎች በዝቅተኛ ገቢ የሚተዳደሩ ዜጎች ላይ ጫና እንዳይፈጥሩ ለደመወዝ፣ ለነዳጅ፣ ለማዳበሪያና ሌሎች መሰረታዊ ድጎማዎች ከ400 ቢሊየን ብር በላይ መመደቡን ገልጸዋል።