ቀጥታ፡

የመዲናዋ ፖሊስ አባላት ከሰላም ማስከበሩ ጎን ለጎን በስፖርቱ ተሳታፊ መሆናቸው ለላቀ ተልዕኮ እንዲዘጋጁ ያግዛል-አቶ ሞገስ ባልቻ

አዲስ አበባ፤ጥር 17/2017(ኢዜአ)፦የአዲስ አበባ ከተማ ፖሊስ አባላት ከሰላም ማስከበሩ ጎን ለጎን በስፖርቱ ዘርፍ ተሳታፊ መሆናቸው ለላቀ ተልዕኮ እንዲዘጋጁ የሚያግዝ አርአያነት ያለው ተግባር መሆኑን በምክትል ከንቲባ ማዕረግ የአዲስ አበባ የዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታ ማስተባበሪያ ማዕከል ኃላፊ አቶ ሞገስ ባልቻ ገለጹ፡፡

በመዲናዋ ተቋርጦ የነበረው የአዲስ አበባ ከተማ አቀፍ የፖሊስ ስፖርታዊ ውድድር እና ፌስቲቫል "ስፖርታዊ እንቅስቃሴ ለላቀ ፖሊሳዊ አገልግሎት" በሚል መሪ ሀሳብ ዛሬ መካሄድ ጀምሯል፡፡

በምክትል ከንቲባ ማዕረግ የአዲስ አበባ የዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታ ማስተባበሪያ ማዕከል ኃላፊ አቶ ሞገስ ባልቻ በዚህ ወቅት እንደተናገሩት፤ አዲስ አበባ የአፍሪካ መዲና እንደመሆኗ መጠን የተለያዩ ዓለም አቀፍ ኮንፍረንሶችና ኩነቶች የሚካሄዱባት ከተማ ናት፡፡

ከዚህ በተጨማሪም ከተማዋ የቱሪስት መዳረሻና የሰላም ተምሳሌት መሆኗንም በማከል፡፡

የፖሊስ አባላት ከህብረተሰቡና ከሌሎችም ፀጥታ አካላት ጋር በመቀናጀት ለከተማዋ ሰላም ተግተው እየሰሩ መሆናቸውን ገልጸዋል።

የፖሊስ ተግባር የአካል ብቃትንና የአዕምሮ ዝግጁነትን የሚጠይቅ ዘርፍ መሆኑን ጠቅሰው፥ አባላቱ ከሰላም ማስከበሩ በተጨማሪም በስፖርቱም ተሳታፊ መሆናቸው ለላቀ ተልዕኮ እንዲዘጋጁ የሚያግዝ አርአያነት ያለው ተግባር ነው ብለዋል፡፡

የአዲስ አበባ ከተማ ፖሊስ አባላት የመዲናዋን ሰላምና ፀጥታ ጠብቃችሁ የሰላም ተምሳሌት እንዳደረጋችሁ ሁሉ በስፖርቱም ተምሳሌት ለማድረግ የድርሻቸውን ሊወጡ እንደሚገባ አሳስበዋል።

የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን ኮሚሽነር ጌቱ አርጋው በበኩላቸው፤ የኢትዮጵያ ስፖርት እድገት አሁን የደረሰበት ደረጃ እንዲደርስ ፖሊስ አባላትና መለዮ ለባሹ ከፍተኛ አስተዋጾኦ ማበርከታቸውን ተናግረዋል፡፡

በኢትዮጵያ ስፖርት ታሪክ ኦሜድላ፣ እርምጃችን፣ መቻል፣ መኩሪያ የተሰኙ የስፖርት ክለቦች ሚለተሪ ለባሹ ለሀገር ስፖርት እድገት ምን ያህል አበርክቶ ማድረጉ ማሳያ ነው ብለዋል፡፡

በዚህም ሀገራችን በዓለም መድርክ ከፍ ያስደርጉ በርካታ ወጤቶች መገኘተቻውን አክለዋል፡፡

በፖሊስ አባላት መካከል የሚደረጉ ስፖርታዊ ውድድሮች በአባላቱ መካከል የእርስ በእርስ ቁርኝት የሚያጠናክሩ ከመሆናቸውም ባሻገር የተለያዩ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ፋይዳ ያለው ተግባር ነው ብለዋል፡፡

ፖሊስ በተለያዩ ዘርፎች እያካሄደ ያለው ስፖርታዊ እንቅስቃሴ እንደተጠበቀ ሆኖ በሁሉም ክፍለ ከተሞች የሚገኙ ፖሊስ አባላትን ያሳተፈ ፌስቲቫል ማዘጋጀት ይህ የመጀመሪያው መሆኑን ኮሚሽነር ጌቱ ገልጸዋል፡፡

ዓላማውም የፖሊስ አባላትን ስፖርታዊ እንቅስቃሴ ከማጠናከር ባለፈ በ19ኛው የፖሊስ ስፖርታዊ ውድድር እና በ5ኛው የምስራቅ አፍሪካ የፖሊስ ስፖርት ውድድር የአዲስ አበባ ፖሊስን ወክለው የሚሳተፉ ብቃት ያላቸውን ስፖርተኞች ለመለየት ነው ብለዋል፡፡

የአዲስ አበባ ወጣቶችና ስፖርት ቢሮ ኃላፊ በላይ ደጀን በበኩላቸው፥ ውድድሩ ከዛሬ ጀምሮ ለተከታታይ 15 ቀናት በስምንት የስፖርት ዓይነቶች እንደሚካሄድ ገልጸው፤ውድድሩ በፍጽም ስፖርታዊ ጨዋነት ሊሆን እንደሚገባም አሳስበዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም