ቀጥታ፡

በለውጡ ዓመታት በተወሰዱ የፖሊሲ እርምጃዎች የአምራች ኢንዱስትሪው ከፍተኛ እመርታ አስመዝግቧል -የኢንዱስትሪ ሚኒስቴር

አዲስ አበባ ፤ ጥር 17/ 2017 (ኢዜአ)፦ በለውጡ ዓመታት የተወሰዱ የፖሊሲ እርምጃዎች የአምራች ኢንዱስትሪው ከፍተኛ እመርታና መነቃቃት እንዲፈጥር ማድረጋቸውን የኢንዱስትሪ ሚኒስቴር አስታወቀ፡፡

መንግሥት ቀጣይነት ያለው የኢኮኖሚ ዕድገት ለመፍጠር፣ ምርቶችን እሴት ጨምሮ ወደ ውጭ ለመላክ፣ ገቢ ምርትን በመተካት የንግድ ሚዛንን ለማስተካከልና ለአስተማማኝ የስራ ዕድል ፈጠራ የያዘውን ግብ ለማሳካት ለአምራች ኢንዱስትሪው ትኩረት ሰጥቷል።

የኢንዱስትሪ ሚኒስትር ዴኤታ ታረቀኝ ቡሉልታ ከኢዜአ ጋር ባደረጉት ቆይታ፤ በ10 ዓመቱ መሪ የልማት ዕቅድ ኢንዱስትሪው የኢኮኖሚው መሪ እንዲሆን የተቀመጠውን የመዋቅራዊ ሽግግር ግብ ለማሳካት ከፖሊሲ ማሻሻያ ጀምሮ ወሳኝ እርምጃዎች መወሰዳቸውን ተናግረዋል።

ምቹ መሰረተ ልማት በመገንባት እና የአሰራር ማሻሻያዎችን በማድረግ መሰረታዊ ለውጥ ያመጡ ተግባራት መከናወናቸውንም አብራርተዋል።

የተኪ ምርት፣ የአምራች ኢንዱስትሪዎች የአቅም ግንባታ፣ የኢንዱስትሪ ኤክስፖርት ምርት ልማትና ሌሎችም ስትራቴጂዎች ተዘጋጅተው  በውጤታማነት እየተተገበሩ ነው ብለዋል።

በዚህም አምራች ኢንዱስትሪው ባለፉት የለውጥ ዓመታት ቀጣይነት ያለው ዕድገት  በማስመዝገብ ላይ እንደሚገኝ ተናግረዋል።

የኢንዱስትሪዎችን የማምረት አቅም ለማሳደግ ዘላቂና ተገማች የግብዓት፣ የኃይል፣ የፕሮጀክትና የኦፕሬሽን ፋይናንስ፣ የካፒታል ዕቃዎች ፋይናንስ አቅርቦትን በከፍተኛ ሁኔታ ማሻሻል ተችሏል ነው ያሉት።

የውጭ ምንዛሬ አቅርቦትም መሻሻሉን ጠቅሰው፥ የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያው የውጭ ምንዛሬ በገበያ እንዲወሰን ማድረጉ ለአምራች ኢንዱስትሪዎች ትልቅ መፍትሔ ማምጣቱንም ተናግረዋል።

ባለፉት የለውጥ ዓመታት የአምራች ኢንዱስትሪዎችን ማነቆዎች በመፍታት የማምረት አቅማቸውን በ2013 በጀት ዓመት ከነበረበት 46 በመቶ አሁን ላይ ወደ 61 በመቶ ማሳደግ መቻሉንም አብራርተዋል።

በሌላ በኩል በአዲሱ ፖሊሲ መሰረት ለወጪና ተኪ ምርቶች እኩል ትኩረት መሰጠቱን ጠቅሰዋል።

በዚህም መሰረት ኢንዱስትሪዎች ከውጭ የሚገቡ 96 የምርት ዓይነቶችን በሶስት ዓመት፣ በአምስት ዓመትና በ10 ዓመት እንዲተኩ ግብ ተይዞ ወደ ሥራ መገባቱን ገልጸዋል።

በዚህም አሁን ላይ የወታደራዊና የተማሪዎች የደንብ ልብሶች፣ የቢራ ብቅል፣ እንደ ፓስታ ያሉና ሌሎች የበለጸጉ ምግቦችን በሀገር ውስጥ  ምርት መተካት መቻሉን ተናግረዋል።

አያይዘውም የሌማት ትሩፋትን ውጤታማ ለማድረግ የመኖ ማቀነባበሪያ ፋብሪካዎችን በሀገር ውስጥ መገጣጠም መጀመሩንም  ገልጸዋል።

ለኮሪደር ልማቱ ስማርት ፖሎችን  በሀገር ውስጥ ማምረት መቻሉም ትልቅ ለውጥ ነው ያሉት አቶ ታረቀኝ፤ በውጭ ምንዛሬ ረገድም ባለፉት ስድስት ወራት ከ2 ቢሊዮን ዶላር በላይ ወጪ ማዳን ተችሏል  ብለዋል።

የሀገር ውስጥ ምርቶች የገበያ ድርሻ ወደ 41 በመቶ ማደጉም የተኪ ምርት ስትራቴጂ ትግበራ ውጤት ነው ያሉት ሚኒስትር ዴኤታው፥ ይህንን አጠናክሮ መቀጠል እንደሚገባ ገልጸዋል።

በሌላ በኩል  በለውጡ ዓመታት የአምራች ኢንዱስትሪውን የኢንቨስትመንት ፍሰት ለማሻሻል ምቹ ከባቢ፣ መሰረተ ልማት፣ የአሰራርና የፖሊሲ ማሻሻያዎች መደረጋቸውንም ጠቅሰዋል።

በዚህም የኢንቨስትመንት ፍሰቱ እየጨመረ  መምጣቱን በማንሳት፥ ባለፉት ስድስት ወራት ብቻ በአጠቃላይ የውጭና የሀገር ውስጥ ባለሀብቶች 202 ቢሊዮን ብር ኢንቨስትመንት ፈሰስ ማድረጋቸውን ጠቅሰዋል።

በዘርፉ የሀገር ውስጥ ባለሀብቶች ተሳትፎ እያደገ  መሆኑንም ገልጸዋል።

ለአብነትም  ከዚህ ቀደም የውጭ ባለሀብቶች ብቻ ይሰማሩባቸው በነበሩ የኢንዱስትሪ ፓርኮች አሁን ላይ ከ50 በመቶ በላይ የሚሆነው በሀገር ውስጥ ባለሀብቶች መያዙን ተናግረዋል።

የአምራች ዘርፉ በስራ ዕድል ፈጠራ ከፍተኛ ሚና እየተጫወተ ነው ብለዋል።

በለውጡ ዓመታት የተተገበረው የኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ ምርታማነትን በማሳደግ እና የአምራች ዘርፉን ችግሮች በመፍታት ረገድ ከፍተኛ እመርታ ማሳየቱን አስረድተዋል። 

የተዘጉ ትላልቅ ፋብሪካዎች በስፋት ወደ ስራ መመለሳቸውን፣ የመሬት፣ የሃይል፣ የፋይናንስና ሌሎች ችግሮች መፈታታቸውን እና ለኢንዱስትሪዎች ከፍተኛ የገበያ እድል መፈጠሩን ተናግረዋል።

ንቅናቄው በፕሮጀክት ደረጃ ራሱን የቻለ ተቋም ኖሮት እየተተገበረ ነው ያሉት ሚኒስትር ዴኤታው፥ ይህም በ10 ዓመት የትግበራ ጊዜው ኢንዱስትሪውን ወደ ከፍታ እንደሚወስደው ጠቁመዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም