ሀገራዊ ለውጡን ተከትሎ የተደረጉ የህግ ማሻሻያዎች ለሰብዓዊ መብት መከበርና የዴሞክራሲ ተቋማት ግንባታ መጠናከር ትልቅ መሠረት አኑረዋል - ሚኒስትር ሃና አርዓያ ስላሴ - ኢዜአ አማርኛ
ሀገራዊ ለውጡን ተከትሎ የተደረጉ የህግ ማሻሻያዎች ለሰብዓዊ መብት መከበርና የዴሞክራሲ ተቋማት ግንባታ መጠናከር ትልቅ መሠረት አኑረዋል - ሚኒስትር ሃና አርዓያ ስላሴ
አዲስ አበባ፤ ጥር 17/2017(ኢዜአ)፡- ሀገራዊ ለውጡን ተከትሎ የተደረጉ የህግ ማሻሻያዎች በኢትዮጵያ ለሰብዓዊ መብት መከበርና የዴሞክራሲ ተቋማት ግንባታ መጠናከር ትልቅ መሠረት ያኖሩ መሆናቸውን የፍትህ ሚኒስትር ሃና አርዓያ ስላሴ ገለጹ፡፡
ሚኒስትሯ በለውጡ ዓመታት በፍትህ ዘርፉ የተከናወኑ ተግባራትንና የተገኙ ስኬቶችን በማስመልክት ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡
በማብራሪያቸውም ሚኒስቴሩ ሕገ-መንግስቱን እና ሕገ-መንግስታዊ ስርዓቱን ማክብርና ማስከበር፣ የህግ-የበላይነት በሀገሪቱ እንዲሰፍን ማድረግ፣ የወንጀል ሕግን ማስከበርና ማስፈጸም እንዲሁም የመንግስትንና የህዝብን ፍትሐ ብሔራዊ ጥቅም ማስከበር በሚል የተሰጡትን ዋና ዋና ኃላፊነቶች እየተወጣ ይገኛል ብለዋል፡፡
ለውጡን ተክትሎ በፍትህ ዘርፉ ላይ መሠረታዊ የሚባሉ ለውጦች ተከናውነው በርካታ ስኬቶችም መመዝገባቸውን ተናግረዋል፡፡
ከስኬቶቹም መካከል የሕግ እና ተቋማዊ ማሻሻያዎች መደረጋቸውን ጠቁመው በዚህም ለህዝብ የቅሬታ ምንጭ የሆኑና መብቶችን የሚገድቡ ህጎችን በመለየት የማሻሻል ስራዎች መሰራታቸውን ገልጸዋል፡፡
አፋኝ የነበሩና የግለሰብ መብቶችን የሚገድቡ መብቶችን የማሻሻል እንዲሁም ዲሞክራሲያዊ ምህዳሩን ለማስፋት አስፈላጊ የሆኑ ህጎችን በመለየት ሰፊ ማሻሻያዎች መደረጋቸውንም ተናግረዋል፡፡
ለአብነትም የጸረ-ሽብር ሕግ ላይ መሰረታዊ ማሻሻያ መደረጉን፣ የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶችን የሚያስተዳድረው ሕግ፣ የመገናኛ ብዙሃን ሕግን በማሻሻል ስኬታማ ስራዎች መሰራታቸውን ጠቁመዋል፡፡
የፍትህ ስርዓቱን ማጠናከር የሚያስችሉ የህግ ስርዓቶች የተሟሉ እንዲሆኑና የነበሩ ክፍተቶችን በመለየት ትልቅ ማሻሻያዎች መደረጋቸውን ተናግረዋል፡፡
በዚህም የንግድ ሕግ-መድብል በአዲስ መልክ ተዘጋጅቶ መውጣቱን ጠቁመው ይህም ከ50 ዓመታት በላይ በስራ ላይ የነበረና ዘመናዊ የንግድና ኢንቨስትመንት አውዶችን ከግምት ውስጥ ያላስገባ እንደነበር አስታውሰዋል፡፡
ይህም በሀገሪቱ እየተከናወኑ ያሉ ሪፎርሞች ውጤታማ በሆነ መንገድ ለማስተግበር ምቹ ሁኔታን የፈጠር መሆኑንም ጠቁመዋል፡፡
በተጨማሪም የወንጀል ስነ-ስርዓትና ማስረጃ ሕግ መድብልም አሁን ያለውን ነባራዊ ሁኔታ ከግምት ውስጥ ያላስገባና አሁን ላለው የወንጀል ፍትህ አስተዳደር አመቺ የሆነ አስተዳደራዊ ህግ ተረቅቆ በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ለመጽደቅ በሂደት ላይ እንደሚገኝም ተናግረዋል፡፡
ሕጉ ጸድቆ ወደ ስራ ሲገባ በወንጀል አስተዳደር ላይ ትልቅ ፋይዳ ያለው ህግ መሆኑንም ጠቁመዋል፡፡
በሌላ መልኩ የግልግል ዳኝነትን የሚመራ ህግ በአዲስ መልክ መውጣቱን ጠቁመው ክርክሮችን በግልግል እና በሌሎች አማራጮች በመፍታት ፍርድ ቤቶች ላይ ያለውን ጫና የሚያስቀርና አማራጭ የሙግት መፍቻ ስርዓትን የሚያስተዋውቅ ህግ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
በዚህም ሀገራዊ ለውጡን ተክትሎ የተደረጉ የህግ ማሻሻያዎች በኢትዮጵያ ለሰብዓዊ መብት መከበርና የዴሞክራሲ ተቋማት ግንባታ መጠናከር ትልቅ መሠረት ያኖሩ መሆናቸውን ገልጸዋል።
የሃይማኖት ነጻነትና እኩልነትን የሚያረጋግጡ ህጎች መውጣታቸውንና በዚህም ለኢትዮጵያ እስልምና ምክር ቤት እውቅና የሰጠ አዋጅ እና የኢትዮጵያ ወንጌላዊያን አማኞች ካውንስልን ያቋቋመ አዋጅ ተጠቃሽ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡
በህግ ማሻሻያ ላይ ዋና ተጠቃሽ የሆነው የዲሞክራሲ ተቋማትን ለማጠናከር የወጡ ህጎችን ጠቅሰዋል፡፡
ባለፉት ዓመታት የተደራጁ ወንጀሎችን ለመከላከል በተሰራው ስራ ከፖሊስ ጋር በመተባበር የማጣራት ስራዎችን በመስራት የወንጀል ፈጻሚዎች ላይ ተጠያቂነትን ማስፈን መቻሉንም ተናግረዋል፡፡
የኢኮኖሚ ወንጀሎችን በተመለከተም የኦዲት ግኝቶችን መሠረት በማድረግና በሌሎች በተደረጉ ማጣራቶች የኢኮኖሚ ወንጀሎች እንደ ሙስና ባሉት ላይ ተሳትፎ ያላቸው ተጠያቂ እንዲሆኑ የማድረግ ስራዎች መሰራታቸውን ጠቁመዋል፡፡