ትክክለኛ የአየር ፀባይ ትንበያን ተደራሽ በማድረግ በየዘርፉ የልማት ሥራዎችን ለመደገፍ የሚሰራው ሥራ መጠናከር አለበት - አብረሃ አዱኛ(ዶ/ር) - ኢዜአ አማርኛ
ትክክለኛ የአየር ፀባይ ትንበያን ተደራሽ በማድረግ በየዘርፉ የልማት ሥራዎችን ለመደገፍ የሚሰራው ሥራ መጠናከር አለበት - አብረሃ አዱኛ(ዶ/ር)
አዳማ፤ ጥር 17/2017(ኢዜአ)፡- ትክክለኛ የአየር ፀባይ ትንበያን ተደራሽ በማድረግ በማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ዘርፎች የሚከናወኑ የልማት ሥራዎችን ለመደገፍ የሚሰራው ሥራ መጠናከር እንዳለበት የውሃና ኢነርጂ ሚኒስትር ዴኤታ አብረሃ አዱኛ(ዶ/ር) ገለፁ።
በመጪው በልግ የሚኖረውን የአየር ፀባይ ሁኔታ ትንበያ እና የበጋ ወቅት የአየር ፀባይ ትንበያን የሚገመግም የባለድርሻ አካላት መድረክ በአዳማ ከተማ በመካሄድ ላይ ነው።
የውሃና ኢነርጂ ሚኒስትር ዴኤታ አብረሃ አዱኛ(ዶ/ር) በመድረኩ መክፈቻ ላይ እንደገለጹት፤ የኢትዮጵያ ሚቲዎሮሎጂ ኢንስቲትዩት እየሰጠ ያለው የአየር ሁኔታ ትንበያ በተጨባጭ መሬት ላይ ያለውን እውነታ ያመላከተ ነው።
መድረኩ የበጋ ወቅት የአየር ፀባይ ሁኔታ ትንበያ የሚገመገምበትና የመጪው የበልግ ወቅት የአየር ፀባይ ትንበያን በአግባቡ በመጠቀም ተጋላጭነትን ለመቀነስ የሚያግዝ መሆኑን ገልጸዋል።
የአየር ንብረት ለውጥ እያስከተለ ያለው ተፅዕኖ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተባባሰ መሆኑን ጠቁመው ኢኒስቲትዩቱ ከባለድርሻ አካላት ጋር በመተባበር ትክክለኛ የአየር ፀባይ ሁኔታ ትንበያ ተደራሽ ለማድረግ የሚሰራውን ስራ ማጠናከር አለበት ብለዋል።
በተለይ የአየር ጸባይ ትንበያን ተደራሽ በማድረግ በማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ዘርፎች የሚከናወኑ የልማት ሥራዎችን ለመደገፍ እየሰራቸው ያሉ ስራዎች መጠናከር እንዳለባቸው አስገንዝበዋል።
የመጪው የበልግ ወቅት ትንበያ መረጃን ለተጠቃሚዎች በአግባቡ ተደራሽ ለማድረግ ኢንስቲትዩቱና ባለድርሻ አካላት በትብብር ሊሰሩ እንደሚገባም ገልጸዋል።
የኢትዮጵያ ሚቲዎሮሎጂ ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር አቶ ፈጠነ ተሾመ በበኩላቸው፤ ኢኒስቲትዩቱ ከባለድርሻ አካላት ጋር በመተባበር የአየር ፀባይ ትንበያ አቅሙን እያሻሻለና ተአማኒነቱን እያጎለበተ መምጣቱን ተናግረዋል።
የአየር ፀባይ ትንበያን ለተጠቃሚዎች በተለያዩ የመገናኛ ዘዴዎች ተደራሽ እያደረገ መሆኑን ገልጸው፣ በዚህም ከቅድመ ማስጠንቀቂያ ጀምሮ በማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ዘርፎች የሚከናወኑ የልማት ስራዎችን እየደገፈ ይገኛል ብለዋል።
በተያዘው የበጋ ወቅትም ደረቅና ነፋሻማ የአየር ሁኔታ እንዲሁም የቀንና የሌሊት ቅዝቃዜ እንደሚኖር ኢኒስቲትዩቱ በትንበያው ማመላከቱንም አስታውሰዋል።
የመጪው በልግ የአየር ሁኔታ ትንበያን አርሶ አደሩና አርብቶ አደሩን ጨምሮ ለተጠቃሚዎች ተደራሽ ለማድረግ ከባለድርሻ አካላት ጋር በትብብር እየሰራን ነው ሲሉም ገልጸዋል።
ተጠቃሚዎችም የቅድመ ማስጠንቀቂያ የአየር ፀባይ ሁኔታ ትንበያን መረጃ በአግባቡ በመጠቀም ሊደርስ የሚችለውን ተፅዕኖ ቀድሞ መከላከልና መቀነስ እንደሚገባቸውም አስገንዝበዋል።