ቀጥታ፡

ለታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ግንባታ ድጋፋችንን እስከመጨረሻው እናጠናክራለን - የደቡብ ኦሞ ዞን ነዋሪዎች

ጂንካ፤ ጥር 17/2017(ኢዜአ)፡- ለታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ግንባታ ቦንድ በመግዛት የሚያደርጉትን ድጋፍ እስከመጨረሻው አጠናክረው እንደሚቀጥሉ የደቡብ ኦሞ ዞን ነዋሪዎች ተናገሩ።

የዞኑ አስተዳደር በበኩሉ የህብረተሰቡን ተሳትፎ በማጎልበት በሦስት ወር ጊዜ ውስጥ 30 ሚሊዮን ብር ድጋፍ ለማሰባሰብ የንቅናቄ ሥራ እያከናወነ መሆኑን አስታውቋል።

ከአስተያየት ሰጪዎቹ መካከል አቶ አዊኖ ጎኔ አንዱ ሲሆኑ ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ለልጆቼ የማወርሰው አሻራዬ ነው ብለዋል።

አይችሉም ሲባል በራሳችን አቅም ገንብተን አሳይተናል ያሉት አቶ አዊኖ፣ በዞኑ የተጀመረውን ንቅናቄ ተከትሎ ቦንድ መግዛታቸውን ተናግረዋል።

ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ኢትዮጵያውያንን ከጫፍ እስከ ጫፍ በልማትና በአብሮነት ያስተሳሰረ መሆኑን የገለጹት ወይዘሮ የምስራች አልዮም በአሁኑ ወቅትም ቦንድ በመግዛት ድጋፍ ማድረጋቸውን ጠቅሰዋል።

የሕዳሴው ግድብ ወደ መጨረሻው ምዕራፍ መሸጋገሩ ልዩ ደስታ እንደፈጠረባቸውም ገልጸዋል።

የደቡብ ኦሞ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ማዕከል ማሊኮ ለሕዳሴው ግድብ የማጠቃለያ ግንባታ ህብረተሰቡን በማስተባበር ድጋፍ ለማድረግ የንቅናቄ ሥራ እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል።

በዚህም በሦስት ወራት ጊዜ ውስጥ ከ30 ሚሊዮን ብር በላይ ገቢ ለማሰባሰብ ታቅዶ እየተሰራ መሆኑን ነው የገለጹት።

ለሕዳሴው ግድብ ግንባታ የመሰረት ድንጋይ ከተቀመጠበት ጊዜ አንስቶ በዞኑ በኩል ድጋፍ ሲደርግ መቆየቱን አንስተው፣ የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎችን በማስተባበር የሚደረገው ድጋፍ እስከመጨረሻው ይቀጥላል ብለዋል።

በመጪው ግንቦት ወር ወደ ደቡብ ኦሞ ዞን የሚገባውን ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ዋንጫ ምክንያት በማድረግ የሀብት ማሰባሰብ ተግባሩ አጠናክሮ ለማስቀጠል ዝግጅት እየተደረገ መሆኑም ተመልክቷል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም