በደሴ ከተማ በለውጡ የተገኙ አበረታች ውጤቶች ይበልጥ ተጠናክረው ይቀጥላሉ - አቶ ሳሙኤል ሞላልኝ

ደሴ፤ ጥር 17/2017(ኢዜአ)፡- በደሴ ከተማ ከለውጡ ወዲህ ህብረተሰቡን በማሳተፍ በተከናወኑ የልማት ተግበራት የተገኙ አበረታች ውጤቶች ይበልጥ ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ የከተማው አስተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ አቶ ሳሙኤል ሞላልኝ ገለጹ።

የከተማውን ልማት ለማሳደግ አስተዳደሩ እያደረገ ያለው ጥረት የሚበረታታ መሆኑን ነዋሪዎች ተናግረዋል።

የአስተዳደሩ ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ሳሙኤል ሞላልኝ፤ ደሴ ከተማ ጥንታዊና ታሪካዊ ከተማ ብትሆንም በእድሜዋና በሚገባት ልክ አለመልማቷን ተናግረዋል፡፡

የለውጡ አመራር አባላት ከህብረተሰቡ ጋር በመቀናጀት ሰፋፊ የልማት ሥራዎችን በማከናወን የከተማዋን ትንሳኤ እያበሰረ መሆኑን ጠቁመው፤ በዚህም ተጨባጭ ውጤት ማስዝገብ ተችሏል ነው ያሉት፡፡


 

በዚህም የህዝቡ የዘመናት ጥያቄ የነበሩ የአስፋልት መንገድ፣ የአንድ ማዕከል አገልግሎት፣ የአውቶቡስ መናኸሪያ፣ የሥራ ዕድል መፍጠሪያ ሼዶች፣ ሌማት ትሩፋትና ሌሎች ሰው ተኮር ፕሮጀክቶችን ማከናወን እየተቻለ ይገኛል ብለዋል።

ከእነዚሁ ፕሮጀክቶች ተጠናቀው ለአገልግሎት የበቁ እንዳሉ ገልጸው፤ የኤሌክትሪክ መስመር ማስፋፋት፤ የፍሳሽ ቆሻሻ ማስወገጃና የኮሪደር ልማት ፕሮጀክቶች ግንባታ በመፋጠን ላይ መሆኑን ተናግረዋል።

እንደ ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባው ማብራሪያ፤ የለውጡ አመራር ለህዝብ የገባውን ቃል በተግባር እየፈጸመ ይገኛል፡፡

በተለይ በፍጥነትና ጥራት እየተከናወነ ያለው የኮሪደር ልማት ከተማዋን በዘላቂነት ምቹ ከማድረግ ባለፈ የቀጣይ ሁለተናዊ እድገትን የሚያሳልጥ ሆኖ እየተከናወነ ነው ብለዋል።

ልማቱ አሁን ላለው ትውልድ ብቻ ሳይሆን የቀጣዩንም ታሳቢ ያደረገ በመሆኑ ለቱሪዝም፣ ለነዋሪዎችና ለኢንቨስትመንት ምቹ ሁኔታ እንደሚፈጥር ገልጸዋል፡፡

የኮሪደር ልማቱ ከአስፋልት መንገድ በተጨማሪ የእግረኛና የብስክሌት መንገድ፣ የአረንጓዴ ልማት፣ የመዝናኛና የዘመናዊ መንገድ ዳር መብራት ዝርጋታንም ያካተተ ነው ሲሉም አመላክተዋል።

በለውጡ የተጀመሩ የልማት ስራዎች የህብረተሰቡን የነቃ ተሳትፎ በመጨመር የበለጠ ተጠናክሮ እንደሚቀጥልም አስታውቀዋል።

ከደሴ ከተማ ነዋሪዎች መካከል አቶ ሰይድ ኡመር በሰጡት አስተያየት፤ ከለውጡ ወዲህ በደሴ ከተማ የተሰሩ ልማቶችና የተገኙ ውጤቶች አበረታችና ተጠናክረው መቀጠል ያለባቸው መሆኑን ተናግረዋል፡፡


 

የዘመናት የልማት ጥያቄዎች እየተመለሱ መሆኑን አንስተው፤ በተለይ የአስፋልት መንገድ፣ የአውቶቡስ መናኸሪያ ግንባታና የደሴ ሙዚየም እድሳት ምላሽ ካገኙ የልማት ፕሮጀክቶች መካከል እንደሚገኙበት ጠቅሰዋል፡፡

የልማት ስራዎች የበለጠ ውጤታማ እንዲሆኑና አዳዲስ የልማት ጥያቄዎችን ማስተናገድ እንዲቻል የከተማዋን ሰላም ከመጠበቅ ባለፈ ልማቱ ላይ በመሳተፍ የድርሻቸውን እንደሚወጡም ተናግረዋል፡፡

የአመራር አባላቱ ከህብረተሰቡ ጋር ተቀናጅተው ወደ ኋላ ቀርታ የነበረችውን ከተማችንን ልማት ለማሳደግ እያደረጉት ያለው ጥረት የሚበረታታ ነው ያሉት ደግሞ ሌላዋ የከተማው ነዋሪ ወይዘሮ መብራት ፈለቀ ናቸው፡፡

የኮሪደር ልማቱና ሌሎችም ፕሮጀክቶች የከተማውን ገጽታ በመቀየር እድገቷን ከፍ የሚያደርግ ነው ሲሉም ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም