ቀጥታ፡

በ971 ወረዳዎች ለሀገራዊ ምክክሩ ግብዓት የሚሆኑ አጀንዳዎችን የማሰባሰብ ስራ ተሰርቷል - ኮሚሽኑ

አዲስ አበባ፤ ጥር 17/2017(ኢዜአ)፡- በኢትዮጵያ በ971 ወረዳዎች ለሀገራዊ ምክክሩ ግብዓት የሚሆኑ አጀንዳዎችን የማሰባሰብ ስራ ማከናወኑን የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ገለጸ፡፡

ኮሚሽኑ በኢትዮጵያ መሰረታዊ በሆኑ ጉዳዮች ላይ የሚስተዋሉ ልዩነቶችና አለመግባባቶች ወሳኝ ምክንያቶችን በሕዝባዊ ውይይቶች በመሰብሰብ፣ በተለዩ አጀንዳዎች ላይ ሀገራዊ ምክክሮችን በማካሄድ፣ ለሀገራዊ መግባባት ምቹ ሁኔታ እንዲፈጠር እየሰራ ይገኛል።

ኮሚሽኑ በሀገሪቱ እስካሁን ያከናወናቸውን ተግባራትና በቀጣይ በሚያከናውናቸው ስራዎች ዙሪያ ኢዜአ የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ቃል-አቀባይ አቶ ጥበቡ ታደሰን አነጋግሯል።

ኮሚሽኑ በኢትዮጵያ መሰረታዊ እና ሀገራዊ በሆኑ አጀንዳዎች ላይ በማህበረሰቡ ዘንድ ያሉ የሀሳብ ልዩነቶችና አለመግባባቶች መንስኤዎችን መለየት የሚያስችል አጀንዳ በመቅረጽ ምክክር እንዲደረግባቸው ማድረግ ነው።

በዚህም ልዩነት በተፈጠረባቸው ጉዳዮች ላይ የጋራ መግባባት የሚፈጠርበትን ምቹ ሁኔታ ለመፍጠር እየሰራ መሆኑን ገልጸዋል።

ኮሚሽኑ በክልሎችና ከተማ አስተዳደሮች በምክክሩ የሚሳተፉ የህዝብ ውክልና ያላቸውን ተሳታፊዎች የመምረጥ እና በተለያዩ ርዕሰ ጉዳዮች ሀገራዊ መግባባት ሊፈጠርባቸው ይገባል የሚሏቸውን አጀንዳዎች የመሰብሰብ ስራ በአብዛኛው አካባቢዎች በስፋት ተሰርቷል ብለዋል።

በዚህም ለሀገራዊ ምክክሩ ግብዓት የሚሆኑ አጀንዳዎች እና የህዝብ ተወካዮችን የመለየት ስራ በአስር ክልሎች እና በሁለቱ ከተማ አስተዳደሮች መካሄዱን አንስተዋል።

በተካሄደው የአጀንዳ ማሰባሰብ ሂደትም ከ18ሺህ በላይ የማህበረሰብ ተወካዮች ኮሚሽኑ በተለያየ ቦታዎች ባካሄደው የአጀንዳ ማሰባሰብ ሂደት ላይ ንቁ ተሳታፊ እንዲሆኑ መደረጉን ጠቅሰው፤ በሀገሪቱ 971 ወረዳዎችም ለምክክሩ ግብዓት የሚሆኑ አጀንዳዎችን የማሰባሰብ ስራ መከናወኑን ገልጸዋል።

በሂደቱም ህዝቡ ለሀገሪቱ ሁለንተናዊ ሰላምና እድገት ማነቆ ናቸው ያላቸውን ሀሳቦችና በሀገር ደረጃ መግባባት ሊፈጠሩባቸው ይገባል የሚላቸውን በርካታ አጀንዳዎች ለኮሚሽኑ ማቅረቡን ተናግረዋል።

በቀጣይም አጀንዳ ማሰባሰብ ባልተከናወነባቸው ክልሎች የማሰባሰብ ሂደቱን ለማከናወን ከሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ጋር በቅንጅት እየተሰራ መሆኑን አብራርተዋል።

በተለያዩ የውይይት መድረኮች እና በልዩ ልዩ አማራጮች ከማህበረሰቡ ከተሰበሰቡ አጀንዳዎች መካከል በዋናው ሀገራዊ ምክክር የጋራ መግባባት ሊፈጠርባቸው የሚገቡ ርዕሰ ጉዳዮችን የመለየት ስራ በቀጣይ እንደሚሰራም አንስተዋል።

ለዚህም እስካሁን የተሰበሰቡ አጀንዳዎችን በአግባቡ የማደራጀትና ተገቢነታቸውን የመፈተሽ ስራ በመስራት ላይ መሆኑን ነው የተናገሩት።

አቶ ጥበቡ አክለውም በየደረጃው ያሉ ኢትጵያውያንም ለሀገራዊ ምክክሩ ስኬታማነት ከፍተኛ አስተዋጽኦ እያደረጉ መሆኑን ጠቅሰው፤ በቀጣይም አጠናክረው እንዲቀጥሉ ጥሪ አቅርበዋል።

እስካሁን ሀገራዊ ምክክር ለማካሄድ በሚደረጉ እንቅስቃሴዎች ተሳታፊ ያልሆኑ የፖለቲካ ፓርቲዎች ሌሎች ባለድርሻ አካላት በጉዳዩ ላይ በመሳተፍ የበኩላቸውን አበርክቶ እንዲያደርጉ ጠይቀዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም