ቀጥታ፡

ኢትዮጵያ ለቀጣናው ብልፅግና በጋራ ተጠቃሚነት መርህ የመሪነት ሚናዋን እየተወጣች ነው - አምባሳደር ነብያት ጌታቸው

አዲስ አበባ፤ ጥር 17/2017(ኢዜአ)፡- ኢትዮጵያ ብሔራዊ ጥቅሟን ከማስከበር ባለፈ ለቀጣናው ብልፅግና በጋራ ተጠቃሚነት መርህ የመሪነት ሚናዋን እየተወጣች መሆኑን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ አምባሳደር ነብያት ጌታቸው ገለጹ።

የኢትዮጵያ የውጭ ግንኙነት ፖሊሲ ብሔራዊ ጥቅምን ያስከበረ ለአፍሪካ ቀንድ እና አጎራባች ሀገራት ትብብር፣ የጋራ ብልፅግና፣ ሰላምና መረጋጋት ቅድሚያ የሚሰጥ መሆኑን ተናግረዋል።

ኢትዮጵያ ከጎረቤት ሀገራት ህዝቦች ጋር እጅ ለእጅ ተያይዛ የጋራ ዕድገትንና ቀጣናዊ ትስስርን የማጠናከር ጽኑ አቋሟን በተግባር እየገለጠች እንደሆነም ጠቁመዋል።

በተጨማሪም ለአፍሪካ አንድነት እና ብልፅግና መሳካት የጋራ ተጠቃሚነት መርህን በማስቀደም እየሰራች እንደምትገኝ ገልጸዋል።

ኢትዮጵያ በዓለም አቀፍ መድረኮች ብሔራዊ ጥቅሟን የሚያስከብሩ ዲፕሎማሲያዊ ተግባራትን እያከናወነች ነው ያሉት ቃል አቀባዩ፥ በዚህም አዳዲስ ስብስቦችን እየተቀላቀለች ነው ብለዋል።

በዚህም ከእያንዳንዱ ጥምረት አባል ሀገራት ጋር የሁለትዮሽና የባለ ብዙ ወገን ትብብሯን የሚያጠናክር ዲፕሎማሲን እየተከተለች መሆኑን አመላክተዋል።

ኢትዮጵያ ለህዝቧ ፍላጎትና ተጠቃሚነት ይበጃሉ ብላ የምትወስዳቸው እርምጃዎች ሁሉ የውጭ ግንኙነት ፖሊሲዋን መሰረት ያደረጉ መሆናቸውንም አንስተዋል።

አምባሳደር ነብያት አያይዘውም ኢትዮጵያ ለ38ኛው የአፍሪካ ህብረት የመሪዎች ጉባኤ ሰፊ ዝግጅት እያደረገች ነው ብለዋል።

ዝግጀቱ እንደ አስተናጋጅ ሀገር የሚጠበቅባትን ኃላፊነት ለመወጣትና እንደ አባል ሀገር ደግሞ በጉባኤው በንቃት የምትሳተፍባቸውና የምታንጸባርቃቸው አጀንዳዎች ላይ ትኩረት ያደረገ መሆኑን ተናግረዋል።

የህብረቱ የመሪዎች ጉባዔ “አፍሪካውያን እና ትውልደ አፍሪካውያን ለተፈጸመባቸው ታሪካዊ ወንጀሎች እና ግፎች ካሳ እንዲያገኙ በማድረግ ለተጎጂዎች ፍትህን ማስፈን” በሚል መሪ ሀሳብ በህብረቱ ዋና መቀመጫ አዲስ አበባ የካቲት 8 እና 9/2017 ዓ.ም ይካሄዳል።

ቀደም ብሎ ደግሞ 46ኛው የአፍሪካ ሕብረት የስራ አስፈጻሚ ምክር ቤት ስብስባ የካቲት 5 እና 6 ቀን 2017 ዓ.ም ይከናወናል።

የመሪዎች ጉባዔ በተለያዩ የአህጉሪቱ አጀንዳዎች ላይ በመምከር ውሳኔዎችን ያሳልፋል ተብሎ ይጠበቃል።

የአፍሪካ ህብረት ኮሚሽን ሊቀመንበር እና ምክትል ሊቀመንበር እንዲሁም የህብረቱ ስድስት ኮሚሽነሮች ምርጫ ይካሄዳል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም