ቀጥታ፡

የፋርማሲዩቲካል ፎረም መቋቋም የሀገር ውስጥ መድሀኒት አቅርቦትን ለማሻሻል የጎላ ሚና አለው - ጤና ሚኒስቴር 

አዲስ አበባ፤ ጥር 16/2017(ኢዜአ)፦ የፋርማሲዩቲካል ፎረም መቋቋም የሀገር ውስጥ መድሀኒት አምራቾች የሚገጥሟቸውን ችግሮች በመቅረፍ የመድሃኒት አቅርቦት እጥረትን መፍታት እንደሚያስችል ጤና ሚኒስቴር ገለፀ። 

በኢትዮጵያ የመድሃኒት አቅርቦት ላይ የሚስተዋሉ ችግሮችን በመፍታት ለመድሃኒት አቅርቦት መሻሻል የሚሰራ ፋርማሲዩቲካል ፎረም በይፋ ተቋቁሟል።


 

ፎረሙ ከ13 የመንግሥት ተቋማትና ዘጠኝ የግል ሴክተሮች የተውጣጡ ባለድርሻ አካላት የተካተቱበት ነው። 

የፎረሙ መቋቋም የሀገር ውስጥ የመድሃኒት አቅርቦትን ለማሻሻል ከሚመለከታቸው አምራቾችና ባለድርሻ አካላት ጋር በቅንጅት መስራት የሚያስችል መሆኑም በዚሁ ጊዜ ተገልጿል።

የጤና ሚኒስትር ዴኤት ፍሬህይወት አበበ እንደገለጹት፤ የሀገር ውስጥ የመድኃኒት ምርትን ለማሳደግና አምራቾችን ለመደገፍ ከፖሊሲ ማሻሻያ ጀምሮ በርካታ ስራዎች ተሰርተዋል።

ለመድሃኒት አምራቾች ምቹ መሰረተ ልማት በማሟላት ረገድ የቂሊንጦ ኢንዱስትሪ ፓርክ ትልቅ ሚና እየተጫወተ መሆኑን ጠቁመው፤ በቀጣይ በዘርፉ የተመዘገቡ ውጤቶችን አጠናክሮ ለማስቀጠል በቁርጠኝነት ይሰራል ብለዋል።

መንግስት ባለፉት ዓመታት የሀገር ውስጥ የመድሀኒት ምርት ድርሻ እንዲጠናከር በሰጠው ትኩረት የሀገር ውስጥ የመድሃኒት ምርት ድርሻ ቀድሞ ከነበረበት 8 በመቶ ወደ 36 በመቶ ማደጉን ተናግረዋል፡፡

ፎረሙ የተገኘውን ውጤት ለማጠናከር የፋርማሲዩቲካል ዘርፍ አቅምን ለማሳደግና የኢንቨስትመንት ፍሰትን ለመጨመር፣ የአምራቾችን ችግሮች በተቋማዊ አደረጃጀት ለመቅረፍ እንደሚያግዝ ጠቁመዋል።


 

የኢንዱስትሪ ሚኒስትር ዴኤታ ታረቀኝ ቡሉልታ መንግሥት ለተኪ ምርት ከሰጠው ትኩረት አንዱ መድሃኒት ነው ብለዋል።

መንግስት የመድሃኒት ማምረትን ውጤታማ የሚያደርጉ የፖሊሲ ማሻሻያና ሌሎች የድጋፍ ተግባራትን እያከናወነ መሆኑን ገልጸዋል።


 

የኢትዮጵያ መድሃኒትና ህክምና መገልገያ መሳሪያዎች አምራች ዘርፍ ፕሬዝዳንትና የክሊችትሮ መድሃኒት ፋብሪካ ባለቤት ዶክተር ዳንኤል ዋቅቶሌ የፎረሙ መቋቋም ከውጭ የሚገቡ መድሃኒቶችን በሀገር ውስጥ ምርት ለመተካት በሚደረገው ጥረት ትልቅ አስተዋፅኦ እንደሚኖረው ጠቁመዋል።


 

የአፍሪኪዩር ኢትዮጵያ የመድሃኒት ፋብሪካ ባለቤት ዶክተር ታደሰ ተፈሪ፥ መንግስት ለጤናው ዘርፍ ትኩረት በመስጠት እየሰራቸው ያሉ ስራዎች አበረታች መሆናቸውን አንስተዋል።   

ለመድሃኒት አምራቾች የውጭ ምንዛሬ በማቅረብ ጥራቱን የጠበቀ መድሃኒት እንዲያመርቱ እያደረገ ነው ብለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም