ቀጥታ፡

ኢትዮጵያ፣ ታንዛንያ እና ኬንያ የሶስትዮሽ የኃይል ሽያጭ ስምምነት ተፈራረሙ

አዲስ አበባ፤ ጥር 16/2017(ኢዜአ)፦ ኢትዮጵያ፣ ታንዛንያ እና ኬንያ የሶስትዮሽ የኤሌክትሪክ ኃይል ሽያጭ ስምምነት ተፈራርመዋል።

በሚያዚያ ወር ወደ ትግበራ የሚገባው ይህ ስምምነት ለቀጣናዊ የንግድና ኢኮኖሚ ትስስር ያለው ፋይዳ የጎላ ነው ተብሎለታል።

የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል፣ የታንዛኒያ የኤሌክትሪክ አቅራቢ ኩባንያ እና የኬንያ የኤሌክትሪክ ማስተላለፊያ ኩባንያ የሶስትዮሽ የኃይል ሽያጭ ድርድር ሲያደርጉ ቆይተዋል። 


 

ተቋማቱ ሲያደርጉት የነበረውን የሶስትዮሽ ድርድር እና ግምገማ አጠናቀው ስምምነቱን መፈራረማቸውን ከኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል የተገኘው መረጃ ያሳያል።

በዚሁ መሰረት ኢትዮጵያ ከታንዛኒያ ጋር የኃይል ሽያጭ እንዲሁም ኬንያ ከታንዛንያ ጋር የኃይል ማስተላለፊያ መስመር የኪራይ ውል ሥምምነት ተፈራርመዋል።

ሥምምነቱን የተፈራረሙት የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል የህግ መምሪያ ዳይሬክተር አቶ መርክነህ ይገዙ፣ የኬንያ የኤሌክትሪክ ማስተላለፊያ ኩባንያ (KETRACO) ስትራቴጂ ሥራ አስኪያጅ ጎድፍሬይ ካሪዩኪ እና የታንዛኒያ የኤሌክትሪክ አቅራቢ ኩባንያ (TANSCO) የዕቅድ፣ ምርምር እና ኢንቨስትመንት ምክትል ዳይሬክተር ሬንታ ንድጌ ተፈራርመዋል።

የኃይል ሽያጭ ሥምምነቱ በሀገራቱ ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች ፀድቆ ከሚያዝያ 2017 ዓ.ም ጀምሮ ተግባራዊ እንደሚደረግ ተገልጿል።

በሥምምነቱ መሰረት ኢትዮጵያ ለታንዛኒያ 100 ሜጋ ዋት የኤሌክትሪክ ኃይል ሽያጭ ታከናውናለች። 

የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል የህግ መምሪያ ዳይሬክተር አቶ መርክነህ ይገዙ ሀገራቱ የሦስትዮሽ ድርድሩን ለማሳካት ላደረጉት ጥረት ምስጋናቸውን አቅርበዋል። 


 

የሦስትዮሽ ሥምምነቱ ከኃይል ሽያጭ ባለፈ ለቀጣናዊ የንግድና ኢኮኖሚ ትስስር ፋይዳው የጎላ ነው ብለዋል። 

ከዚህ ቀደም በኢትዮጵያና ኬንያ መካከል የኃይል ሽያጭ ውል ሥምምነት ተፈርሞ ተግባራዊ እየተደረገ እንደሚገኝ ያወሱት ዳይሬክተሩ ከኃይል ሽያጩም ከፍተኛ የውጭ ምንዛሬ ማግኘት መቻሉን ጠቁመዋል።

ስምምነቱ ኢትዮጵያ በኬንያ በኩል ለታንዛኒያ የኤሌክትሪክ ኃይል ሽያጭ ለማከናወን የሚያስችላትን መብት የሚሰጣት መሆኑንም ነው ዳይሬክተሩ ያብራሩት።

የታንዛኒያ የኤሌክትሪክ አቅራቢ ኩባንያ የዕቅድ፣ ምርምር እና ኢንቨስትመንት ምክትል ዳይሬክተር ሬንታ ንድጌ ድርድሩ በተሳካ ሁኔታ በመጠናቀቁ ደስታቸውን ገልጸው ተቋማቱ ለተግባራዊነቱ በቁርጠኝነት እንዲሰሩ አሳስበዋል።

የኬንያ የኤሌክትሪክ ማስተላለፊያ ኩባንያ ስትራቴጂ ሥራ አስኪያጅ ጎድፍሬይ ካሪዩኪ በበኩላቸው የሦስትዮሽ የኃይል ሽያጭ ድርድሩ በተሳካ ሁኔታ እንዲጠናቀቅ ላደረጉት የተቋማቱ ባለሙያዎች ምስጋናቸውን ማቅረባቸውን ከተቋሙ የተገኘው መረጃ ያመለክታል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም