ኢትዮጵያ እና ብራዚል በአሳ ሃብት ልማት ትብብር መፍጠር የሚያስችላቸውን ውይይት አደረጉ - ኢዜአ አማርኛ
ኢትዮጵያ እና ብራዚል በአሳ ሃብት ልማት ትብብር መፍጠር የሚያስችላቸውን ውይይት አደረጉ
አዲስ አበባ፤ ጥር 16/2017(ኢዜአ)፡- በብራዚል የኢትዮጵያ አምባሳደር ልዑልሰገድ ታደሰ ከብራዚል የአሳ ሃብት ሚኒስትር አንድሬ ዳ ፓውላ ጋር ተወያይተዋል።
ውይይቱ በሀገራቱ መካከል የአሳ ሃብትን ለማልማት የሚያስችል ትብብር መፍጠር ላይ ያተኮረ መሆኑን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር መረጃ ያመለክታል።
አምባሳደር ልዑልሰገድ የአሳ ሃብት ልማት በኢትዮጵያ የልማት ፓሊሲ ትኩረት ከተሰጣቸው የእድገት አቅሞች መካከል አንዱ መሆኑን ገልጸዋል።
በኢትዮጵያ የግብርና ዘርፍን በማዘመን እና ምርታማነትን በማሳደግ የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ የሚደረገው ጥረት ከፍተኛ እመርታ እያሳየ ነው ብለዋል።
አምባሳደሩ ከብራዚል ጋር በአሳ ሃብት ልማት ትብብር መፍጠር ቀጣይነት ላለው እድገት ወሳኝ አበርክቶ እንደሚኖረው ተናግረዋል።
የብራዚል የአሳ ሃብት ሚኒስትር አንድሬ ዳ ፓውላ ብራዚል ሁለቱ ሀገራት በግብርና ዘርፍ ያላቸውን ትብብር በአሳ ሃብት ልማት ዘርፍ እንዲጠናከር የማድረግ ፍላጎት እንዳላት ገልጸዋል።
ብራዚል በአሳ ሃብት ልማት ያካበተችውን ልምድን ፣ ቴክኖሎጂ እና እውቀት በሁለትዮሽ ትብብር እና በብሪክስ ማዕቀፍ ለኢትዮጵያ ለማካፈል ዝግጁ መሆኗን ተናግረዋል ።