መንግስት ለባህል ዘርፍ ዕድገት ትኩረት ሰጥቷል-የባህልና ስፖርት ሚኒስትር ሸዊት ሻንካ - ኢዜአ አማርኛ
መንግስት ለባህል ዘርፍ ዕድገት ትኩረት ሰጥቷል-የባህልና ስፖርት ሚኒስትር ሸዊት ሻንካ
አዲስ አበባ፤ጥር 16/2017(ኢዜአ)፦መንግስት ለባህል ዘርፍ ጥበቃና ዕድገት በትኩረት እየሠራ መሆኑን የባህልና ስፖርት ሚኒስትር ሸዊት ሻንካ ገለጹ።
በኦሮሚያ ክልል ባህልና ቱሪዝም ቢሮ የተዘጋጀ የ72ኛው የቦረና ገዳ ሥርዓት የባሊ ርክክብን በተመለከተ የፓናል ውይይት በአዲስ አበባ ተካሂዷል።
በመድረኩ የባህልና ስፖርት ሚኒስትር ሻዊት ሻንካ፣የኦሮሚያ ክልል ባህል እና ቱሪዝም ቢሮ ኃላፊ ጀሚላ ሲምቢሩ፣ የኦሮሚያ ክልል ፕሬዚዳንት ጽህፈት ቤት ኃላፊ አብዱላዚዝ ዳውድ (ዶ/ር)፣ አባገዳዎች፣ ሀዳሲንቄዎች እና ሌሎች ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ተገኝተዋል።
የቦረና ገዳ የባሊ ርክክብ ከየካቲት 25 እስከ 30 ቀን 2017 ዓ.ም በተለያዩ ዝግጅቶች በምስራቅ ቦረና በአሬሮ ወረዳ በአርዳ ጂላ በዳሳ ይከናወናል ተብሏል።
የባህልና ስፖርት ሚኒስትር ሸዊት ሻንካ፥ ሚኒስቴሩ የሀገሪቱ ባህልና እሴቶች ተጠብቀው እንዲቆዩ እየሰራ ይገኛል ብለዋል።
የገዳ ሥርዓት ተጠብቆ እንዲቆይ የኦሮሞ አባገዳዎች ላበረከቱት አስተዋፅኦ ምስጋና እንደሚገባቸው የገለጹት ሚኒስትሯ፤ መንግስት የባህል ዘርፍ እንዲጠበቅና እንዲጠናከር በትኩረት እየሰራ እንደሚገኝም ተናግረዋል፡፡
የኦሮሚያ ባህልና ቱሪዝም ቢሮ ኃላፊ ጀሚላ ሲምቢሩ በበኩላቸው፥ የገዳ ሥርዓት ዴሞክራሲያዊ የአስተዳደር ሥርዓትን ለዓለም ያበረከተና በሰላማዊ መንገድ የስልጣን ሽግግር የሚደረግበት ነው ብለዋል።
የክልሉን ባህል የማስተዋወቅ እና እሴቱ ተጠብቆ ለቀጣይ ትውልድ እንዲተላለፍ የማድረግ ሥራዎች እየተሰሩ እንደሚገኙ ጠቁመዋል።
የገዳ ሥርዓት በክልሉ በሚገኙ ትምህርት ቤቶች እንደ አንድ ትምህርት እየተሰጠ መሆኑን ገልጸው፥ ይህም ልጆች ስለባህላቸውና ስለዴሞክራሲ እንዲያውቁ የሚያስችል መሆኑን አንስተዋል።
የኦሮሚያ ክልል ፕሬዚዳንት ጽህፈት ቤት ኃላፊ አብዱላዚዝ ዳውድ (ዶ/ር) ገዳ የኦሮሞ ሕዝብ የፖለቲካ፣ የአስተዳደርና የማህበራዊ ሥርዓት ነው ብለዋል።
ይህ ሥርዓት ለትውልድ እንዲተላለፍ ለማድረግ ምሁራን በጥናትና ምርምር ሊያግዙ እንደሚገባ ገልጸዋል።
71ኛው የቦረና አባገዳ ኩራ ጃርሶ በገዳ ሥርዓት መሰረት ባሊን/ሥልጣናቸውን በደስታና በፍቅር ለማስረከብ መዘጋጀታቸውን ገልጸዋል።
"እኛ ባሊን በደስታ ለማስረከብ ተዘጋጅተናል፣የኢትዮጵያ ህዝብ በቦታው ተገኝቶ ስርዓቱን እንዲታደም ጥሪ እናቀርባለን" ብለዋል።
72ኛው የቦረና አባገዳ የሚሆኑት ጎዮ ቦሩ በበኩላቸው፥ በሥርዓቱ መሰረት ባሊ/ሥልጣን ለመቀበል እየተዘጋጁ መሆኑን ተናግረዋል።
በገዳ ሥርዓት መሰረት ሁሉንም ደረጃዎች በማለፍ አባገዳ ለመሆን መብቃታቸውን ገልጸው፥ በሥርዓቱ መሰረት በአግባቡ ለመምራት እንደተዘጋጁ ገልጸዋል።
የገዳ ሥርዓት በ2009 ዓ.ም በተባበሩት መንግስታት የትምህርት፣ የሳይንስ እና የባህል ድርጅት (ዩኔስኮ) የማይዳሰስ ቅርስነት የተመዘገበ የዓለም ቅርስ ነው።