ቀጥታ፡

ሔር ኢሴ በዓለም ወካይ ቅርስነት መመዝገቡ ባህላዊ ሀብቶችና ቅርሶች እንዲታወቁ የተጀመሩ ጥረቶች እንዲጠናከሩ የሚያግዝ ነው -ሚኒስትር ሰላማዊት ካሳ

ድሬደዋ፤ ጥር 16/2017(ኢዜአ)፦"ሔር ኢሴ" በዓለም ወካይ ቅርስነት መመዝገቡ የኢትዮጵያ ባህላዊ ሀብቶችና ቅርሶች በአለም አደባባይ እንዲታወቁ የተጀመሩ ጥረቶች እንዲጠናከሩ የሚያግዝ መሆኑን የቱሪዝም ሚኒስትሯ ሰላማዊት ካሳ ተናገሩ።

''ሔር ኢሴ'' በተሰኘው የኢሳ ማህበረሰብ ባሕላዊ መተዳደሪያ ሕግ ላይ ያተኮረ የፓናል ውይይት በድሬደዋ ከተማ እየተካሄደ ነው።

በፓናል ውይይቱ ላይ የተገኙት የቱሪዝም ሚኒስትሯ ሰላማዊት ካሳ፤ የአለም ቅርስ የሆነው ''ሔር ኢሴ'' በአፍሪካ ቀንድ አገራት ህዝቦች መካከል ያለውን ትስስር እና አንድነት በማፅናት በኩል የሚኖረው አበርክቶ የጎላ መሆኑን አንስተዋል።

በተጨማሪም በአካባቢው ዘላቂ ሰላም፣ልማት እና የጋራ ዕድገት ለማስመዝገብ ከፍተኛ ሚና እንዳለው ገልጸዋል።

እንደ ሚኒስትሯ ገለፃ ''ሔር ኢሴ'' በዓለም ቅርስነት መመዝገቡ በቀጣይ የሌሎች አካባቢዎች ባህሎችና ቅርሶች በዓለም አቀፍ ደረጃ እንዲታወቁ ለማድረግ የሚያግዝ ነው።

"ሔር ኢሴ " በውስጡ ብዙ ተጠንተው ለአደባባይ መገለጥ እና ጥቅም ላይ መዋል ያለባቸው ጥልቅ ጉዳዮች ያሉት መሆኑን ጠቅሰው፥ እነዚህ እሴቶች ተተንትነው እንዲገለፁ ሚኒስቴሩ በትኩረት እንደሚሰራም አስታውቀዋል።

"ሔር ኢሴ" ህዳር 26/2017 ዓ.ም በፓራጓይ ዋና ከተማ አሱንሲዮን በተካሄደው 19ኛው የተባበሩት መንግሥታት የትምህርት፣ የሳይንስና የባሕል ድርጅት (ዩኔስኮ) የሰው ልጆች ወካይ የማይዳሰስ የዓለም ቅርስ ሆኖ መመዝገቡ ይታወሳል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም