ቀጥታ፡

በድሬደዋ ሳብያን ጠቅላላ ሆስፒታል የተገነባው የድንገተኛ ህሙማን ማዕከል አገልግሎት መስጠት ጀመረ

ድሬደዋ፤ጥር 16/2017(ኢዜአ)፦በድሬደዋ ሳብያን ጠቅላላ ሆስፒታል የተገነባው የድንገተኛ ህሙማን መታከሚያ ማዕከል ተመርቆ አገልግሎት መስጠት ጀምሯል።

ማዕከሉን፥ የጤና ሚኒስትር ዶክተር መቅደስ ዳባ፣የድሬደዋ አስተዳደር ምክር ቤት አፈ ጉባኤ ወይዘሮ ፈትህያ አደንና የድሬደዋ አስተዳደር ከንቲባ ከድር ጁሃር መርቀው ስራ አስጀምረውታል።

የጤና ሚኒስትር ዶክተር መቅደስ ዳባ በወቅቱ እንደተናገሩት፥ አገራዊ ለውጡ የጤና አገልግሎት ተደራሽነት በማስፋት፣ የበሽታ መከላከልና አክሞ የማዳን ተልዕኮ ስኬታማ እየሆነ ነው።

በድሬደዋ ሳብያን ሆስፒታል የተገነባው የድንገተኛ ህክምና አገልግሎት ማዕከልም የዚሁ ተልእኮ ማሳኪያ መሆኑን ጠቅሰዋል።

እንደ ዶክተር መቅደስ ገለፃ፥ በመላው አገሪቱ የጤና ተቋማት የድንገተኛ ህክምና ማዕከላት የተሟላ አገልግሎት እንዲሰጡ አስፈላጊ
የህክምና መሳሪያዎችን የማሟላት ተግባራት እየተከናወኑ ነው።

የድሬደዋ አስተዳደር ከንቲባ ከድር ጁሃር በበኩላቸው፥ አገራዊ ለውጡን ተከትሎ በገጠርና በከተማ ፍትሃዊ የጤና ተደራሽነትን በማረጋገጥ ጥራት ያለው አገልግሎት በማቅረብ በኩል አበረታች ውጤት እየታየ ነው።

ማዕከሉም፥ ከከተማዋ በዘለለ ለምስራቁ የኢትዮጵያ ክፍል አገልግሎት የሚሰጥ በመሆኑ ተልዕኮውን እንዲያሳካ ሚኒስቴሩ እገዛ እንዲያደርግ ጠይቀዋል።

የድሬደዋ አስተዳደር ጤና ቢሮ ኃላፊ ዶክተር ፅጌረዳ ክፍሌ በበኩላቸው፥ ሆስፒታሉ ለበርካታ ህሙማን አገልግሎት እንደሚሰጥ ተናግረዋል።

አሁን አገልግሎት የጀመረው የድንገተኛ ህክምና መስጫ ማዕከልም ዘመናዊና ጥራት ያለው የድንገተኛ ህክምና አገልግሎቶችን ለሁሉም ተደራሽ ለማድረግ አጋዥ መሆኑን ጠቅሰዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም