የኢትዮጵያ ሆስፒታሎች ጥምረት ጥራት እና ደህንነቱ የተጠበቀ አገልግሎት ለመስጠት አቅም ፈጥሯል-ሚኒስቴሩ - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያ ሆስፒታሎች ጥምረት ጥራት እና ደህንነቱ የተጠበቀ አገልግሎት ለመስጠት አቅም ፈጥሯል-ሚኒስቴሩ
አዳማ፤ጥር 16/2017 (ኢዜአ)፦የኢትዮጵያ ሆስፒታሎች ጥምረት ጥራት እና ደህንነቱ የተጠበቀ የጤና አገልግሎት ለመስጠት አቅም መፍጠሩን የጤና ሚኒስቴር ገለጸ።
በሚኒስቴሩ አዘጋጅነት ''የኢትዮጵያ ሆስፒታሎች ጥምረት ለጥራት'' የ2017 በጀት ዓመት ግማሽ ዓመት የአፈጻጸም ግምገማ መድረክ በአዳማ እየተካሄደ ነው።
በመደረኩ ላይ የተገኙት የጤና ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር ደረጄ ዱጉማ፥ ሚኒስቴሩ የህክምና አገልግሎት ጥራት ማሻሻያ ፕሮግራሞችን ነድፎ ለተግባራዊነቱ በቅንጅት እየሰራ መሆኑን ገልጸዋል።
በተለይ “የኢትዮጵያ ሆስፒታሎች ጥምረት ለጥራት” ፕሮግራም ጥሩ ተሞክሮ ያላቸው ሆስፒታሎች ልምዳቸውን እንዲያካፍሉና እንዲደጋገፉ እያደረገ ነው ብለዋል።
ይህም ጥራቱና ደህንነቱን የተጠበቀ የጤና አገልግሎት በሁሉም ጤና ተቋማት ለመስጠት አቅም መፍጠሩን አስረድተዋል።
በተለይ ሳንባ ነቀርሳ፣ ኤች አይቪ ኤድስና ወባን ከሌሎችም የጤና ፕሮግራሞች ጋር ተቀናጅተው በሁሉም የጤና ተቋማት ደረጃ እየተሰጡ መሆኑን ተናግረዋል።
ፕሮግራሙ ሀብትን በመቆጠብ የተሻለ አገልግሎት ለመስጠት የመተባበርና የውድድር መንፈስ እንዲኖር ገንቢ ሚና መጫወቱን ገልጸዋል።
ይህም በውጭ እርዳታ ላይ የተንጠለጠለውን የጤና ሴክተር በውስጥ አቅም ለመሸፈን ማገዙንም ዶክተር ደረጀ አስታውቀዋል።
ጥምረቱ ለሆስፒታሎች የግብዓት እና የበጀት ድጋፍ መስራቱንም ጠቅሰዋል።
ባለፉት ስድስት ወራት የጤና ሚኒስቴር የጤና ተቋማትን ለማደራጀት አምቡላንስና ሌሎች ግብአቶችን በማሟላት በተለይ የድንገተኛ ክፍሎችን በግብዓትና በሰው ሃይል በማብቃት ላይ በርካታ ስራዎች መከናወናቸውን አብራርተዋል።
አዳዲስ እስፔሻሊቲና ሳብ እስፔሻሊቲ ፕሮግራም ለመክፈትም በግማሽ በጀት ዓመቱ ጥረት መደረጉን አመልክተዋል።
በሚኒስቴሩ የህክምና አገልግሎት መሪ ሥራ አስፈጻሚ ዶክተር ኢሉባቦር ቡኖ በበኩላቸው፥ ጥምረቱ የሆስፒታሎችን ትስስር በማጠናከር ፍትሃዊና የተቀናጀ የህክምና አገልግሎትን በሁሉም ደረጃ ተደራሽ ለማድረግ ከፍተኛ አስተዋጽኦ እያበረከተ ይገኛል።
ለሁለት ቀናት በተዘጋጀው መድረክ ላይ የጤና ሚኒስቴር ኃላፊዎች፣ የክልል ጤና ቢሮ ከፍተኛ አመራር አባላትና ተወካዮች እንዲሁም በየደረጃው የሚገኙ የሆስፒታሎች ኃላፊዎችና ባለድርሻ አካላት እየተሳተፉ ናቸው።