ቀጥታ፡

በክልሉ ግብርናን በማዘመን የአርሶ አደሩ ተጠቃሚነት እንዲጎለብት ድጋፍ ተደርጓል

መቀሌ፤ ጥር 16/2017(ኢዜአ)፡- በትግራይ ክልል የእርሻ ሜካናይዜሽንን በማስፋፋት ዘመናዊ የግብርና አሰራርን በመዘርጋት የአርሶ አደሩ ተጠቃሚነት እንዲጎለብት ድጋፍ ማድረጉን የኢትዮጵያ የግብርና ትራንስፎርሜሽን ኢንስቲትዩት ገለጸ።

ኢንስቲትዩቱ ድጋፍ ያደረገው ባለፈት ሁለት የምርት ዓመታት መሆኑን ገልፀዋል። 

በኢትዮጵያ የግብርና ትራንስፎርሜሽን ኢንስቲትዩት የትግራይ ክልል የእርሻ ሽግግር ማዕከል ዳይሬክተር አብረሃ ኪዳነ ማርያም(ዶ/ር) ለኢዜአ እንደገለፁት፤ ኢንስቲትዩቱ በእርሻ ዘርፍ የተለያዩ ፕሮጀክቶችን ቀርፆ ለአርሶ አደሮች ተጠቃሚነት እየሰራ ነው።

የክልሉን ግብርና ለማዘመን፣ የምርጥ ዘር አቅርቦት ለማሻሻልና የማር ምርትን ለማሳደግ ባለፉት ሁለት ዓመታት ውጤታማ ተግባራት መከናወናቸውን ገልፀዋል።


 

ኢንስቲትዩቱ ክላስተርን መሰረት አድርገው ለተደራጁ ሞዴል አርሶ አደሮች ለሚገኙባቸው ስድስት ወረዳዎች 18 ዘመናዊ ትራክተሮችን ድጋፍ ማድረጉን ጠቁመው፤ እንዲሁም ሌሎች 16 ወረዳዎችን ተጠቃሚ ያደረጉ ምርትና ምርታማነትን መጨመር የሚያስችሉ ድጋፎች መከናወናቸውን አስረድተዋል።

በእነዚሁ ወረዳዎች ከ96 ሺህ በላይ አርሶ አደሮችን ተጠቃሚ ያደረገ ከ17 ሺህ ኩንታል በላይ ምርጥ ዘር መከፋፈሉን አውስተው፤ ይህም ለክልሉ የእርሻ ሜካናይዜሽን እና ምርታማነትን ለማሳደግ አስተዋጽኦ ማድረጉን አመልክተዋል።

በተጨማሪም ኢንስቲትዩቱ በንብ ማነብ፣ በመስኖ ልማት እና በዶሮ እርባታ በኩል በሚያደርጋቸው ድጋፎች 10 ሺህ የሚሆኑ አርሶ አደሮች ተጠቃሚ መሆናቸውን ጠቁመዋል።

በክልሉ የሚገኙ የእርሻ ምርምርና ማሰልጠኛ ማዕከላት እንዲሁም የምርጥ ዘር ብዜት ዩኒየኖችን ለአራት ዓመታት ተጠቃሚ የሚያደርጉ ፕሮጀክቶችን ከሐምሌ 2017 ዓ.ም ጀምሮ ተግባራዊ እንደሚደረግም አመልክተዋል።

ኢንስቲትዩቱ የክልሉ አርሶ አደሮችን ተጠቃሚ የሚያደርጉ ፕሮጀክቶችን የመደገፍ ተግባሩን አጠናክሮ እንደሚቀጥልም ዳይሬክተሩ አረጋግጠዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም