ቀጥታ፡

ኢትዮጵያና ፓኪስታን የንግድ ዘርፍ ትብብራቸውን ለማጠናከር ተወያዩ

አዲስ አበባ፤ ጥር 16/2017(ኢዜአ)፦ ኢትዮጵያና ፓኪስታን የሁለትዮሽ የንግድ ዘርፍ ትብብራቸውን ማጎልበት በሚያስችሉ ጉዳዮች ላይ ተወያዩ።

የንግድ እና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስትር ካሳሁን ጎፌ (ዶ/ር) በፓኪስታን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የአፍሪካ ሀገራት ዋና ኃላፊ አምባሳደር ሃሚድ አስጋር ከተመራ ልዑክ ጋር ተወያይተዋል።

ሚኒስትሩ ውይይቱ በሁለቱ ሃገራት የሁለትዮሽ የንግድ ግንኙነት ላይ ያተኮረ መሆኑን በማህበራዊ ትስስስር ገጻቸው ባሰፈሩት መልዕክት ገልጸዋል።

ፓኪስታንና ኢትዮጵያ ዘመናትን የተሻገር ሁለንተናዊ ግንኙነት እንዳላቸው ገልጸው የሀገራቱ ህዝብ ብዛትና የማምረት አቅምም በመጠቀም የላቀ ውጤት ማስመዝገብ እንደሚቻል የጋራ መግባባት ላይ መደረሱን አመልክተዋል።

አምባሳደር ሃሚዲ ኢትዮጵያ ላሳየችው የውጭ ንግድ ዕድገት በማድነቅ በቀጣይ የኢትዮጵያ ምርቶች በፓኪስታን ገበያ በስፋት እንዲቀርቡ ለማመቻቸት ቃል ገብተዋል ነው ያሉት ሚኒስትሩ በመልዕክታቸው።

ፓኪስታን በግንቦት ወር 2017 ዓ.ም በአዲስ አበባ ለምታዘጋጀው ኤክስፖ ኢትዮጵያ ድጋፍ እንደምታደርግም ጠቁመዋል።

ኢትዮጵያ እና ፓኪስታን ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነታቸውን እ.አ.አ በ1973 እንደጀመሩ መረጃዎች ያመለክታሉ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም