የሀገራዊ ቅርሶችን ኢኮኖሚያዊ አበርክቶ ማጎልበት የሚያስችሉ የቅርስ ጥበቃና ጥገና ስራዎች እየተከናወኑ ነው - ኢዜአ አማርኛ
የሀገራዊ ቅርሶችን ኢኮኖሚያዊ አበርክቶ ማጎልበት የሚያስችሉ የቅርስ ጥበቃና ጥገና ስራዎች እየተከናወኑ ነው
አዲስ አበባ፤ ጥር 16/2017(ኢዜአ)፦ በኢትዮጵያ የሀገራዊ ቅርሶችን ኢኮኖሚያዊ አበርክቶ ማጎልበት የሚያስችሉ የቅርስ ጥበቃና ጥገና ስራዎች እየተከናወኑ መሆኑን የኢትዮጵያ ቅርስ ባለስልጣን ገለፀ።
የጊፋታ በዓልን ለዩኔስኮ ለማስመዝገብ ሠነድ ሲልክ፤ ለጣና ገደማትና አካባቢው ደግሞ ሠነድ ዝግጅት ላይ መሆኑንም ባለስልጣኑ አስታውቋል።
በባለስልጣኑ የብሔራዊ ሙዚየም መሪ ስራ አስፈፃሚ አንዱአለም ግርማይ ለኢዜአ እንዳሉት የቅርሶች ጥበቃና እንክብካቤ ለትውልድ ከማሻገር ባለፈ ለኢኮኖሚ እና ለገጽታ ግንባታ አይተኬ ሚና አላቸው።
በሀገር በቀል የኢኮኖሚ ሪፎርሙ ከአምስት የኢኮኖሚ ምሰሶዎች አንዱ ቱሪዝም መሆኑን ጠቅሰው፤ ታሪካዊ ቅርሶች ደግሞ ለቱሪዝም መሰረቶች ናቸው ብለዋል።
በመሆኑም የሀገራዊ ቅርሶችን ኢኮኖሚ አበርክቶ ለማጎልበት የሚያስችሉ የቅርስ ጥበቃና ጥገና ስራዎች እየተከናወኑ መሆኑን አንስተዋል።
ባለስልጣኑ ተንቀሳቃሽ፣ ቋሚ እና የማይዳሰሱ ባሕላዊ ቅርሶችን በየፈርጁ ለይቶ የጥበቃና የማልማት ስራዎችን እያከናወነ ስለመሆኑ ጠቁመዋል።
ከሀገራዊ ታሪካዊ ቅርሶች መካከል የጎንደር፣ ጅማ አባጅፋርና የቤንሻንጉል ጉምዝ ክልል የሚገኘው የደጃዝማች መሀመድ ባንጃው አብያተ መንግሥታት እና የድሬዳዋ ምድር ባቡር ዕድሳት እየተደረገ መሆኑን ለአብነት ጠቅሰዋል።
ቅርሶች የትናንት መመልከቻ ሕያው ምስክር በመሆናቸው ማደስና ማልማትና ለተተኪው ትውልድ ማስተዋወቅ ወሳኝ መሆኑን ጠቅሰዋል።
ለአብነትም በቅርቡ ዕድሳቱ የተጠናቀቀው የብሔራዊ ቤተ መንግስት የፖለቲካ፣ የኢኮኖሚ፣ ማህበራዊና ዲፕሎማሲያዊ ታሪኮች ማሳያ በመሆኑ የሚኖረውን ሁለንተናዊ አበርክቶ ጠቅሰዋል።
ኢትዮጵያ እስካሁን 17 የሚዳሰሱና የማይዳሰሱ ቅርሶችን በተባበሩት መንግስታት የትምህርት፣ የሣይንስ እና የባሕል ድርጅት (ዩኔስኮ) ማስመዝገቧን አስታውሰዋል።
የወላይታ የዘመን መለወጫ ጊፋታ በዓልን ለማስመዝገብ የሰነድ ዝግጅት ተጠናቆ ለዩኔስኮ መላኩን አስታውሰው፤ የጣና ገደማትና አካባቢውን ለማስመዝገብ ደግሞ ሰነድ እየተዘጋጀ መሆኑን ገልጸዋል።
ህብረተሰቡና ባለድርሻ አካላት ህገ ወጥ የቅርስ ዝውውርን መከላከልና ቅርስ ጥገና ስራ ላይ መሳተፍ እንዳለበት ጥሪ አቅርበዋል።