ቀጥታ፡

ኮሚሽኑ በዘመኑ ቴክኖሎጂ የሚመራ የጭነት እንቅስቃሴ መከታተያ ስርዓት ሊተገብር ነው

አዲስ አበባ፤ ጥር 16/2017(ኢዜአ)፦ ጉምሩክ ኮሚሽን በድንበር የሚተላለፉ የጭነት እና የዕቃ እንቅስቃሴዎችን በዘመኑ ቴክኖሎጂ የሚቆጣጠር 'ኤሌክትሮኒክ ካርጎ ትራኪንግ ስርዓት'ን ተግባራዊ ሊያደርግ መሆኑ ተገለጸ።

ስርዓቱ የአገልግሎት አሰጣጥ ለማዘመንና ሕጋዊ ቁጥጥርን ለማጠናከር አስተዋጽኦ እንዳለው ተመላክቷል።

በኤሌክትሮኒክ ካርጎ ትራኪንግ ስርዓት፣ በሰው ሰራሽ አስተውሎት መሰረት አድርጎ የድንበር ቁጥጥር እንዲሁም ሌሎች የቴክኖሎጂ ውጤቶች ልማትና ትግበራ ላይ ያተኮሩ ውይይት ተካሄዷል።

በውይይቱ ላይ የጉምሩክ ኮሚሽን ኮሚሽነር ደበሌ ቃበታ፣ የአርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ወርቁ ጋቸና (ዶ/ር)፣ የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የፕሮጀክቶቹ ስራ አስኪያጅ ሽብሩ ተመስገን (ዶ/ር) እና ሌሎች የኮሚሽኑ አመራሮች ተገኝተዋል፡፡

ኮሚሽነር ደበሌ ቃበታ እንዳሉት የኮሚሽኑን አገልግሎት አሰጣጥ ለማዘመንና የህግ ተገዥነትን ለማረጋገጥ የሚያስችሉ ቴክኖሎጂዎችን ተግባራዊ እያደረገ ነው።

ከአርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ኢንስቲትዩት እና ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ጋር በመቀናጀት የኤሌክትሮኒክ ካርጎ ትራኪንግ ስርዓትን ጨምሮ ቴክኖሎጂዎችን ወደ ሙሉ ትግበራ ለማሸጋገር እየተሰራ ነው ብለዋል።

የአርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ወርቁ ጋቸና (ዶ/ር) በበኩላቸው፤ ኢንስቲትዩቱ የኮሚሽኑን አገልግሎት የሚያሳልጡ ዘርፈ ብዙ የቴክኖሎጂ ውጤቶችን እያለማ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

የኢትዮጵያ ኤሌክትሮኒክ ካርጎ ትራኪንግ ስርዓት እና ሌሎች ቴክኖሎጂዎችን ወደ ሙሉ ትግበራ ለማሸጋገር ከፍተኛ ርብርብ እየተደረገ ነው ብለዋል።

በውይይቱ የኢትዮጵያ ኤሌክትሮኒክ ካርጎ ትራኪንግ ስርዓት እና ሌሎች ቴክኖሎጂዎች በአጭር ጊዜ ውስጥ ስራቸው ተጠናቆ ወደ ትግበራ እንደሚገባ ከገቢዎች ሚኒስቴር የተገኘው መረጃ ያመለክታል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም