ጤና ሚኒስቴር፣ የኢትዮጵያ አየር መንገድ እና ኸርት አታክ ኢትዮጵያ በትብብር መስራት የሚያስችላቸውን የመግባቢያ ሰነድ ተፈራረሙ - ኢዜአ አማርኛ
ጤና ሚኒስቴር፣ የኢትዮጵያ አየር መንገድ እና ኸርት አታክ ኢትዮጵያ በትብብር መስራት የሚያስችላቸውን የመግባቢያ ሰነድ ተፈራረሙ
አዲስ አበባ፤ ጥር 15/2017(ኢዜአ)፦ ጤና ሚኒስቴር፣ የኢትዮጵያ አየር መንገድ እና ኸርት አታክ ኢትዮጵያ በትብብር መስራት የሚያስችላቸውን የሶስትዮሽ የመግባቢያ ሰነድ ተፈራርመዋል።
የጤና ሚኒስትር ዶክተር መቅደስ ዳባ፤ ለሶስተኛ ዙር ነጻ የልብ ቀዶ ህክምና ለማድረግ ወደ ኢትዮጵያ የመጣውን የሃኪሞች ቡድን ተቀብለው አወያይተዋል።
ቡድኑ እየሰጠ ስለሚገኘው በጎ ተግባር በተገልጋዩ ህብረተሰብ ስም ምስጋና ያቀረቡት ሚኒስትሯ የስምምነቱ መፈረም በኢትዮጵያ የሚሰጠውን የልብ ህክምና ለማሳደግ እንደሚረዳ ገልጸዋል፡፡
ኸርት አታክ ኢትዮጵያ ከጤና ሚኒስቴር እንዲሁም ከኢትዮጵያ አየር መንገድ ጋር በትብብር መስራት የሚያስችለውን የመግባቢያ ሰነድ መፈረሙ የሀኪሞች ቡድኑ የሚሰጣቸውን የበጎ ፍቃድ አገልግሎቶች ለማስፋት እንደሚረዳ የድርጅቱ ስራ አስኪያጅ ዶክተር ኦብስኔት መርዕድ ተናግረዋል።
በተጨማሪም ኢትዮጵያውያን ሀኪሞችን ለማሰልጠን እንደሚረዳም ጨምረው መግለጻቸውን የጤና ሚኒስቴር መረጃ ያመላክታል፡፡
እንደ ከዚህ ቀደሙ ሁሉ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ከጤና ሚኒስቴር ጋር በትብብር መስራቱን እንደሚቀጥል የኢትዮጵያ አየር መንገድ ዋና ስራ አስኪያጅ ተወካይ አቶ ለማ ያደቻ መግለጻቸውም ተጠቁሟል።
ኸርት አታክ ኢትዮጵያ ለሚሰጠው አገልግሎት አየር መንገዱ ድጋፍ እንደሚያደርግም ተናግረዋል፡፡
የስምምነቱ መፈረም በኢትዮጵያ እየተሰጠ የሚገኘውን የልብ ህክምና አገልግሎት ለማሻሻል እንደሚረዳ በፊርማ መርሃ-ግቡሩ ተገልጿል፡፡