ለታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ድጋፋችን ተጠናክሮ ይቀጥላል - የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ጤና ቢሮ አመራሮችና ሠራተኞች - ኢዜአ አማርኛ
ለታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ድጋፋችን ተጠናክሮ ይቀጥላል - የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ጤና ቢሮ አመራሮችና ሠራተኞች
ጂንካ ፤ ጥር 15/2017(ኢዜአ)፦ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ግንባታ እስኪጠናቀቅ ድረስ የምናደርገውን ድጋፍ አጠናክረን እንቀጥላለን ሲሉ የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ጤና ቢሮ አመራር አባላትና ሠራተኞች ገለፁ።
የአመራር አባላት እና ሠራተኞቹ ለታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ ማስፈፀሚያ የሚውል የ261 ሺህ ብር የቦንድ ግዢ ዛሬ ፈጽመዋል።
የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል መንግስት ጤና ቢሮ ኃላፊ አቶ እንዳሻው ሽብሩን ጨምሮ የቢሮው ማኔጅመንት አባላት እና ሠራተኞች በቦንድ ግዢ ማርሃ-ግብሩ ላይ ተገኝተዋል።
የቢሮው ኃላፊ አቶ እንዳሻው ሽብሩ በወቅቱ እንደገለፁት፤ የታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ የአብሮነታችን እና የጥንካሬያችን ማሳያ በመሆኑ ግንባታው እስኪጠናቀቅ ድረስ ድጋፋችን ይጠናከራል ሲሉም ነው የገለጹት።
አቶ እንዳሻው አክለውም፤ ቀሪውን የግንባታ ሥራ ለማጠናቀቅ እንደ ከዚህ ቀደሙ ቦንድ በመግዛት ደማቅ አሻራችንን በድጋሚ እያኖርን ነው ብለዋል።
የቢሮው ምክትል ኃላፊ አቶ ነብዩ ቤዛ በበኩላቸው፤ ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ግንባታን በአብሮነት ማሳካት መቻላችን የዚህ ትውልድ አድዋ መሆኑን ገልጸዋል።
ከቢሮ ሠራተኞች መካከል ወይዘሮ ዝናሽ ካሳ በበኩላቸው በሰጡት አስተያየት፤ ለታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ድጋፍ ተጠይቆ ወደ ኋላ የሚል እንደማይኖር ተናግረዋል።
ግንባታው ከተጀመረበት ጊዜ አንስቶ ከደመወዛቸው ቦንድ በመግዛት ድጋፍ ሲያደርጉ መቆየታቸውን ጠቅሰው፤ የሕዳሴው ግድብ አለኝታችንና ሀገራዊ ኩራታችን በመሆኑ ግድቡ እስኪጠናቀቅ ድረስ ድጋፋችን አይቋረጥም ብለዋል።