ቀጥታ፡

የበይነ መረብ ግብይት ስርዓቱ ፈጣንና አካታች ኢኮኖሚን ለማሳካት ያግዛል- ሚኒስትር ካሳሁን ጎፌ(ዶ/ር)

አዲስ አበባ፤ ጥር 15/2017(ኢዜአ)፦ የኢትዮጵያ ምርት ገበያ የበይነ መረብ ግብይት ስርዓት ፈጣንና አካታች ኢኮኖሚን ለማሳካት የሚያግዝ መሆኑን የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስትሩ ካሳሁን ጎፌ(ዶ/ር) ገለጹ።

ሚኒስትሩ የኢትዮጵያ ምርት ገበያ ዘመናዊ የንግድ ስርዓት ለማሳለጥ የሚያስችሉ ተግባራትን ይፋ ያደረጉ ሲሆን አንዱ የበይነ መረብ ግብይት ስርዓት ነው።


 

የበየነ-መረብ (ኦንላይን) ግብይት የሀገርን ግብይት ስርዓት ከመሰረቱ የሚቀይርና የንግዱ ዘርፍ በኢኮኖሚ የሚገባውን ድርሻ እንዲወጣ የሚያስችል መሆኑን ተናግረዋል።

የበየነ-መረብ ግብይት ስርዓት ፍትሃዊነትን የሚያረጋግጥና ለወጪ ንግድ ብዝሃነት ትልቅ ግብዓት የሚሆን ነው ያሉት ሚኒስትሩ፤ የግብይት ሰንሰለቱን በማሳጠር ከደላላ የጸዳና አምራችና ነጋዴ ከያሉበት በቀጥታ የሚገናኙበት ስርዓት ነው ብለዋል፡፡

የግብይት ስርዓትን በማዘመን አርሶ አደሮች የአካታች የፋይናንስ ሥርዓት ተጠቃሚ እንዲሆኑ እንደሚያግዝ ገልጸዋል።

በዓለም አቀፍ ደረጃ ውጤታማ የሆኑ አስራሮችን በኢትዮጵያ በማስጀመር ፈጣንና አካታች ኢኮኖሚን ለማሳካትም ያግዛል ነው ያሉት፡፡

ሚኒስትሩ የዲጂታል ግብይትን ጽንሰ ሀሳብ ያነገበ አዲሱን የኢትዮያ ምርት ገበያ መለያ ምልክት (ሎጎ) ይፋ አድርገዋል።

በሌላ በኩል የምርት ገበያው ሁለገብ አገልግሎት የሚሰጥ ባለ24 ወለል ሕንጻ ግንባታ መሰረተ ድንጋይ አስቀምጠዋል።

ሕንጻው ለቀልጣፋና አካታች ግብይት ምቹ የስራ ከባቢን የሚፈጥርና የዲጂታል ገበያ ስርዓቱ ትልቅ ግብዓት እንደሚሆን ገልጸዋል።


 

የኢትዮጵያ ምርት ገበያ ዋና ስራ አስፈጻሚ አቶ ወንድምአገኘሁ ነገራ በበኩላቸው፤ አዲሱ የበይነ መረብ ግብይት የግብርና እና ማዕድናት ምርቶችን በዓለም አቀፍ ደረጃ እንደሚያገበያይ ገልጸዋል።

የበይነ መረብ ቀጥታ ግብይት ተደራሽነትን፣ አሳታፊነትን፣ ግልጸኝነትንና ፍትሃዊነትን እንደሚያጠናከር ጠቁመዋል።

ባለፉት ስድስት ወራት ተልባ፤ የቢራ ገብስና ሌሎች አዳዲስ ምርቶችን ወደ ግብይት ስርዓት መግባታቸውን አስታውሰው፤ በቀጣይ ጨውን ጨምሮ ማዕድናት፣ ቆዳና ሌጦና ሌሎች አዳዲስ ምርቶች በበይነ መረብ ግብይት ስርዓት ይካተታሉ ብለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም