እያደገ የመጣውን የትራንስፖርት ፍላጎት ለመመለስ ጥረት እየተደረገ ነው- ሚኒስቴሩ

አዲስ አበባ፤ ጥር 15/2017(ኢዜአ)፦ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ የመጣውን የህብረተሰቡ ትራንስፖርት ፍላጎትን ለማሟላት የሚያስችሉ ዘርፈ ብዙ ተግባራት እየተከናወኑ መሆኑን የትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ ሚኒስቴር ገለፀ።

የፐብሊክ ሰርቪስ ትራንስፖርት አገልግሎት ከባለድርሻ አካላት ጋር ውይይት አካሄዷል።

የትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ ሚኒስትር ዴኤታ አቶ በረኦ ሀሰን በዚሁ ወቅት እንዳሉት፤ ከለውጡ ወዲህ ውጤታማ ከሆኑ ዘርፎች አንዱ ትራንስፖርት ነው።


 

ትራንስፖርት ለዜጎች የዕለት ከዕለት የስራ እንቅሰቃሴና ማህበራዊ ትስስር በማሳለጥ ካለው አይተኬ ፋይዳ አኳያ ፍላጎቱ ከህዝብ ቁጥር ዕድገት ጋር አብሮ እየጨመረ እንደሚያድግ ገልጸዋል።

በዚህም የትራንስፖርት አገልግሎት ሰጪ ተሽከርካሪዎችን ቁጥር ብቻ ሳይሆን አገልግሎቱ በአይነት፣ በምልልስ መጠን፣ በመንገድ አቅርቦትና ሽፋን ተደራሽነት ላይ በመስራት ፍላጎቱን ለመመለስ ጥረት እየተደረገ ነው ብለዋል።

ለአብነትም በአዲስ አበባ ከተማ እና የፌዴራል ተቋማት ስራተኞች የስራ መግቢያና መውጫ ሰዓት የሰርቪስ አገልግሎት እየሰጠ መሆኑን ገልጸው፤ በትርፍ ሰዓት ባሶቹ በተመጣጣኝ ዋጋ ለህብረሰተቡ የትራንስፖርት አገልግሎት እንዲሰጡ መደረጋቸውን ገልጸዋል።

የፐብሊክ ሰርቪስና ትራንስፖርት አገልግሎት ምቹ፣ አስተማማኝና ፈጣን ለማድረግም በርካታ ማሻሻዎች በመካሄድ ላይ ነውም ብለዋል።

የፐብሊክ ሰርቪስ ትራንስፖርት አገልግሎት ዋና ዳይሬክተር አቶ ጥላሁን ጅግሶ በበኩላቸው፤ አገልግሎቱ 460 በከተማ ሰርቪስ የሚሰጡ እና 50 ልዩ ሀገር አቋራጭ አውቶቡሶች ወደ ስራ በማስገባት ለህብረሰተቡ አገልግሎት እየሰጡ መሆናቸውን ጠቅሰዋል።

ለተሽከሪካሪዎቹ ብልሽት ጥገና፣ ቦሎ ምርምራና ማሰልጠኛ ተግባራትን ተቋሙ በራሱ አቅም እያከናወነ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

በአዲስ አበባ የሚስተዋለውን የአገልግሎት መጨናነቅ ለማቃለል ለሀገር አቋራጭ የተዘጋጁ ዘመናዊ አውቶቡሶችን ወደ አገልግሎቱ ማስገባቱን ጠቅሰዋል።

የመድረኩ ተሳታፊዎች የአውቶቡሶቹ ቁጥር በመጨመር በአንዳንድ አካባቢ የሚስተዋለውን መጨናነቅ መቅረፍ እንደሚገባ ጠይቀዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም